Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ መኮንን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ጸሀፊ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ጸሐፊ አሚና መሀመድ ጋር ተወያይተዋል።
በወቅቱም ዋና ጸሀፊዋ የኢትዮጵያ መንግስት በተለያዩ ጫናዎችን ውስጥ እያለፈ እንኳ ሁኔታዎችን በሰከነ ሁኔታ በመመልከት ከተባበሩት መንግስታት ጋር ያለውን ግንኙነት ገንቢ በሆነ መልኩ ለማስቀጠል ላሳየው ቁርጠኝነት አድናቆታቸውን ገልፀዋል።
አክለውም በአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ለመታደም መምጣታቸውን በሀገሪቱ የአማራ፣ ሶማሌና ትግራይ ክልሎች ጉብኝት በማድረግ በመሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ለመገንዘብ ዕድል እንደፈጠረላቸውም ነው ያመለከቱት።
በጉብኝታቸው በአካባቢዎቹ በተከሰቱ ግጭቶች የደረሰውን ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመቶችን መመልከታቸውን ገልጸዋል።
አያይዘውም በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅ በህብረተሰቡ ላይ ያደረሰውን የጉዳት ደረጃ ለመገንዘብ መቻላቸውንም አንስተዋል።
በሌላ በኩል በሀገሪቱ ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን የተጀመሩ ጥረቶችን ማስቀጠል እንደሚገባ የጠቆሙት ምክትል ዋና ጸሐፊዋ፥ ግጭት በተካሄደባቸው አካባቢዎችም የመልሶ ግንባታ ስራዎች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባም አንስተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው፥ የተባቡሩት መንግስታት ድርጅት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ጠንካራ ግንኙነት ለማስቀጠል ዋና ጸሐፊው እና ሌሎች የድርጅቱ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ላሳዩት ተነሳሽነት ምስጋቸውን ገልጸዋል።
አያያዘውም የተባቡሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያ ላይ ጫናን ለማድረግ ያለሙ ተከታታይ ስብሰባዎችን ማካሄዱ አግባብነት የሌለው መሆኑንም ገልጸዋል።
አቶ ደመቀ የኢትዮጵያ መንግስት በተለያዩ አካባቢዎች የሚደረጉ ሰላምን የማደፍረስ ተግባራትንም እንዲሁም ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚደርግበትን ጫና በማቋቋም አንጻራዊ ሰላም የሰፈነበት ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረግ መቻሉን ለምክትል ዋና ጸሃፊዋ አስረድተዋል።
ሰሞኑን የተካሄደው የአፍሪካ ህብረት ስብሰባን በተሳካ ሁኔታ ተካሂዶ መጠናቀቁም በአብነትነት የሚጠቀስ መሆኑን ነው የገለፁት።
መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ ውሳኔ ማሳለፉን፣ ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ምክክር እንዲደረግ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መከናወኑን እንዲሁም ከማንኛውም ግጭት ቀስቃሽ ተግባራት መታቀቡ፣ የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ እንዲሆን ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠሩ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ያለውን ቁርጠኝነት አመላካች መሆኑን አስረድተዋል።
በህወሓት የሽብር ቡድን በኩል ግን መጀመሪያውንም በሀገሪቱ አጠቃላይ የሰላም መደፍረስ እንዲኖር አቅዶ ሲንቀሳቀስ እንደነበር ገልጸው፥ አሁንም በሚያደርገው ትንኮሳ የእርዳታ አቅርቦት ተደራሽ እንዳይሆን ሆን ብሎ የማወክ ተግባሩ እንደቀጠለበት ነው ብለዋል።
አቶ ደመቀ አያይዘውም በአንዳንድ አካባቢዎች በተከሰተው ድርቅ እንዲሁም በተካሄዱ ግጭቶች ምክንያት በርካታ ህዝብ የስብዓዊ እርዳታን የሚሻ መሆኑን ጠቅሰው፥ መንግስት በየብስም ሆነ በአየር በረራ የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽ እንዲሆን ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
የዓለም አቀፉ ማህበረሰብም የሰብዓዊ እርዳታ በማቅረብ እንዲሁም የመልሶ ማቋቋም ጥረቶችን በመደገፍ የድርሻውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
በመጨረሻም መንግስት ከተለያዩ አካላት ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት በማስቀጠል ተጨባጩን የኢትዮጵያ እውነታ የማስረዳት ተግባሩን አጠናክሮ የሚስቀጠል መሆኑን ለዋና ጸሐፊዋ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽኅፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.