Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስዋሂሊ ቋንቋን ትምህርት ለማስጀመር የመግባቢያ ሰነድ ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና የታንዛንያው ዳሬሰላም ዩኒቨርሲቲ የስዋሂሊ ቋንቋን ትምህርት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለማስጀመር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ።

ስምምነቱን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና እና የዳሬሰላም ዩኒቨርሲቲ ቫይስ ቻንስለር ፕሮፌሰር ዊሊያም አናንጊሴ ተፈራርመውታል፡፡

ስምምነቱ በዋናነት የሚያተኩረው የስዋሂሊን ቋንቋ በምስራቅ አፍሪካ ከሚነገሩት ቋንቋዎች ውስጥ መሪ የመግባቢያ ቋንቋ ለማድረግ ሲሆን ፥ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ቋንቋውን በመጀመሪያ ዲግሪ እና በሁለተኛ ዲግሪ መርሃግብሮች ለማስጀመር ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

በተጨማሪም የአካዳሚክ እና የምርምር መርሃ ግብሮችን በማሳደግ እና በመተግበር ኢኮኖሚያዊ እና ባህላዊ እድገትን በሁለቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል ለማነቃቃት እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የስዋሂሊኛ ቋንቋን ከማስፋፋት ባለፈም በሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል የሁለትዮሽ የአካዳሚክ መርሃግብሮችን ማስፋፋት፣ የስልጠናና የስታፍ ልምድ ልውውጥ ማድረግ፣ የምርምር ትብብር እና የተማሪዎች ክትትልን ማጠናከር እንዲሁም የፒኤችዲ ዲዘርቴሽን የምርምር ተግባር ትብብርን እንደሚያጠቃልል ተመላክቷል፡፡

ስምምነቱ ለአምስት ዓመታት የሚቆይ ሲሆን ፥ እንደአስፈላጊነቱም በሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች መልካም ፈቃደኝነት መሰረት የሚታደስ መሆኑን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.