Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮ – ሱዳን ግንኙነትን ለማጠናከር የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ የሱዳን ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስታወቁ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የተጀመሩ እንቅስቃሴዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ የሱዳን ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር አሊ አል ሳዲቅ አሊ አስታወቁ፡፡

በሱዳን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ ከሱዳን ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር አሊ አል ሳዲቅ አሊ ጋር በሁለትዮሽና ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

በምክክሩ አምባሳደር ይበልጣል በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል ያለውን ለዘመናት የዘለቀ ሁለንተናዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ልዩነት የሚታይባቸውን የድንበር እና የሕዳሴ ግድብ ጉዳዮች ለመፍታት ተቀራርቦ መስራት ተገቢ እንደሆነ አስምረውበታል።

በተጨማሪም መተማ-ገለባት የድንበር ኬላ ለዜጎች እንቅስቃሴ ክፍት እንዲደረግ፣ ወደ አገራቸው ለመመለስ ለሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን በኢሚግሬሽን ባለሥልጣናት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የተጣለው የመውጫ ክፍያ እንዲሰረዝ ወይም የኢትዮጵያዊያኑን ኑሮና ገቢ ሁኔታ ያማከለ እንዲሆን ጥያቄ አቅርበዋል።

ሚኒስትሩ በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል ያለው ግንኙነት በልዩ ሁኔታ የሚታይ መሆኑን ጠቅሰው ፥ በአገራቱ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር የተጀመሩ እንቅስቃሴዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ በመጥቀስ የመተማ-ገለባት ድንበር እንዲከፈትና የመውጫ ቪዛ ጉዳይ እልባት ያገኙ ዘንድ እንደሚሰሩ ገልፀዋል።

በሁለቱ አገራት መካካል ያለውን ግንኙት ካለበት ደረጃ ለማሻሻል የሚስተዋሉ ጅምር እንቅስቃሴዎችን ለማስቀጠል፣ በድንበር እና በሕዳሴ ግድብ ጉዳይ እንዲሁም በሌሎች ስትራቴጂክ ጉዳዮች ዙሪያ ተቀራርቦ ለመነጋገርና የጋራ መፍትሔዎችን ለማበጀት የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎችን ለማከናወን ከመግባባት ላይ መደረሱንም ከኤምባሲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.