የኦሮሚያ ክልል ለአማራ ክልል የ100 ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)የኦሮሚያ ክልል በአማራ ክልል በጦርነቱ ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች የሚውል 100 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርጓል።
የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በአማራ ክልል በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሚውለውን የ100 ሚሊየን ብር ድጋፍ ለአማራ ክልል አስረክበዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ ድጋፉን ሲያስረክቡም ኢትዮጵያ ትልቅ ፈተና ውስጥ እንደሆነችና ይህም ብዙ መፈናቀልና የሰው ሕይወት መጥፋት ያስከተለ መሆነን ተናግረዋል፡፡
አሸባሪው ወራሪ ቡድን ጥቃት የከፈተበት፣ በኦሮሚያ ክልል ያሉ ተላላኪዎችም ጥፋት የፈፀሙበት ነውም ብለዋል ።
በከፍተኛ መስዋእትነት ሀገር ቀጥላለች ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ የተከፈለው ዋጋ ለሀገር የሆነ ቢሆንም ጠባሳው ከባድ መሆኑን አንስተዋል።
የዛሬው ድጋፍም ከአማራ ክልል ጎን መቆማችንን ለማሳየት የተደረገ ነው ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል በሚጠይቃቸው ሁሉ ለማገዝና ክልሉን ከነበረበት ከፍ አድርጎ ለመገንባት ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል፤ ከተጋገዝን እና በአንድነት ከቆምን ፈተናው ከፍ ያደርገናል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ድጋፉን የተረከቡት የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ለተደረገው ድጋፍ አመስግነው፥ የሽብር ቡድኑ ህወሃት የኢትዮያውያን ጠላት መሆኑን አንስተዋል፡፡
አማራ ሲጠቃ የኦሮሚያ ክልል አብሮ መቆሙን ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ኢትዮጵያዊያን አንድ ሆነን በሄድን ጊዜ ጠላታችን እናሸንፋለን ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!