Fana: At a Speed of Life!

ከደቡብ ሱዳን የሚነሱ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች በጋምቤላ ስደተኛ ካምፕ ላይ ጥቃት ማድረሳቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፤የካቲት 3፣2014 (ኤፍ ቢሲ) በጋምቤላ ክልል ከደቡብ ሱዳን የሚነሱ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ድንበር አቋርጠው በመግባት በዲማ ስደተኛ ካምፕና በጎግ ወረዳ ጥቃት ማድረሳቸውን የክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኡገቱ አዲንግ እንደገለጡት ፥ በጥቃቱ የአንድ ሠው ህይወት ሲያልፍ ሁለት ሠዎች ላይ ጉዳት መድረሱንና ሶስት ህፃናት ታፍነው ተወስደዋል።
ክልሉን ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚያጋራው ድንበር ሰፊና ክፍት ስለሆነ ታጣቂዎች በተለያየ ጊዜ ተደጋጋሚ ጥቃት እያደረሱ ይገኛሉ ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪም በጎግ ወረዳ ከፑኝዶ ከተማ ወደ ቴዶ ቀበሌ በሚንቀሳቀስ ሞተር ሳይክል ላይ ባደረሱት ጥቃት የአንድ ሰው ህይወት ማለፉን ነው የተናገሩት።
በቅርቡ መነሻውን ከጋምቤላ ከተማ አድርጎ ወደ ኑዌር ዞን በመጓዝ ላይ ባለ የጭነት መኪና ላይ ማንነታቸው ያልታወቁ ግለሰቦች ባደረሱት ጥቃት የመኪናው አሽከርካሪ እና ረዳቱ ህይወታቸው እንዳለፈም ገልጸዋል።
ጥቃት ያደረሱትን ግለሰቦች የክልሉ ልዩ ኃይልና ሚሊሻዎች ተከታትለው አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ ጠንካራ ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
ህብረተሰቡም ከፀጥታ አካላት ጎን በመሆን አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ አቶ ኡገቱ ጠይቀዋል።
የክልሉ መንግስት በአሁኑ ሰዓት ልዩ ኃይሉንና ሚሊሻውን በመጠቀም ጥቃት በደረሰባቸው አካባቢዎች ሰላምና ፀጥታ የማስከበር ስራውን እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች በየቦታው ሾልከው ሊገቡ ስለሚችሉ ህብረተሰቡ አካባቢውን ነቅቶ ሊጠብቅ እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ምከክልሉ ፕሬስ ሴክሬታሪት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.