Fana: At a Speed of Life!

ቢሮው ከተለያዩ የገቢ አርስቶች ከ11 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት ከተለያዩ የገቢ አርስቶች ከ11 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ ገቢዎች ቢሮ የግብር ትምህርትና የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አጉማስ ጫኔ ለኢዜአ እንደገለጹት ፥ ገቢው የተሰበሰበው በአሸባሪው ህውሓት ወረራ ጉዳት ካልደረሰባቸው የክልሉ አካባቢዎች በተደረገው ጥረት ነው።

ዳይሬክተሩ እንዳሉት ከገቢው ውስጥ ከ10 ቢሊየን ብር በላይ የሆነው የተገኘው ከመደበኛ ገቢ ምንጭ ሲሆን ፥ ቀሪው ከከተማ አገልግሎት ዘርፍ የተሰበሰበ ነው።

በክልሉ ሰባት ዞኖች የተፈጸመው ወረራ ከግምት ውስጥ በማስገባት በሌሎቹ አካባቢዎች የተጠናከረ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

የተሰበሰበው ገቢ ከግማሽ ዓመቱን ዕቅድ 73 በመቶ ያህል ማሳካት እንደተቻለ አቶ አጉማስ ገልጸው ፥ የአሸባሪው ህወሓት ወረራ በገቢ አሰባሰቡ ዕቅድ እንዳይሳካ አድርጎታል ብለዋል።

ከዚህም ባሻገር በጦርነቱ ምክንያት የንግዱ ዘርፍ መቀዛቀዝ፣ ደረሰኝን በአግባቡ የማይቆርጡ ነጋዴዎች መኖራቸውም ለዕቅዱ አፈጻጸም ማነስ ምክንያት መሆናቸውን ገልጸዋል።

ቢሮው በበጀት ዓመቱ ከተለያዩ የገቢ አርስቶች ለመሰብሰብ ያቀደውን ከ30 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ በማሳካት የክልሉን ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማፋጠን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

በባህርዳር ከተማ በጽህፈት መሳሪያዎች ንግድ ዘርፍ የተሰማሩት አቶ ደሳለኝ ገላው በሰጡት አስተያየት በቁርጥ ግብር የሚጠበቅባቸውን 12 ሺህ 500 ብር ግብር በወቅቱ መክፈላቸውን ገልጸዋል።

አቶ ደሳለኝ አክለውም ፥ ክልሉ እንኳንስ ችግር ውስጥ በገባበት ወቅት ቀርቶ በሰላሙም ጊዜ ግብርን በአግባቡና በወቅቱ መክፈል የዜግነት ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን ግዴታም ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.