Fana: At a Speed of Life!

በሙርሌ ታጣቂዎች የታገቱ ህጻናትን ለማስመለስ የፌደራል ፖሊስ ከክልሉ የጸጥታ ሃይል ጋር በመሆን በጋራ እየሰራ ይገኛል – የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል አኝዋክ ዞን ዲማ ወረዳ ኡኩቡ በሚገኘው የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ሰሞኑን ከደቡብ ሱዳን አጎራባች አካባቢ ሰርገው በገቡ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች የታገቱ ህጻናትን ለማስመለስ የፌደራል ፖሊስ ከክልሉ የጸጥታ ሃይል ጋር በመሆን በጋራ እየሰራ እንደሚገኝ የኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ፥  የታገቱትን አምስት ህጻናት ለማስመለስ ከሚደረገው ጥረት ባሻገር በሁለቱም ሃገራት አጎራባች አካባቢዎች የሚኖሩ የሃገር ሸማግሌዎችንና የማህበረሰቦቹን ተወካዮች ባሳተፈ መልኩ ዘላቂ ሰላምን በአካባቢው የማስፈን ጥረት እንደሚቀጥል ነው ያስታወቀው።

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦

“በሙርሌ ታጣቂዎች የታገቱ ህጻናትን ለማስመለስ የፌደራል ፖሊስ ከክልሉ የጸጥታ ሃይል ጋር በመሆን በጋራ እየሰራ ይገኛል” – የመንግስት ኮሙኒኬሽን  አገልግሎት

በጋምቤላ ክልል አኝዋክ ዞን ዲማ ወረዳ ኡኩቡ በሚገኘው የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የካቲት 2  ቀን 2014 ዓ.ም ከለሊቱ በ5 ሰአት ከደቡብ ሱዳን አጎራባች አካባቢ ሰርገው የገቡ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች አምስት ህጻናትን አግተው ወስደዋል።

እነዚሁ ታጣቂዎች በስደተኞች ጣቢያው በከፈቱት ተኩስም ሁለት ሴቶችን አቁስለዋል።

በተመሳሳይ በቀጣዩ ቀን ማለትም የካቲት 3 ቀን 2014 ዓ.ም ዳግም ታጣቂዎቹ በጎግ ወረዳ በከፈቱት ጥቃት የአንድ ግለሰብ ህይወት አልፏል።

በስፍራው የተፈጠረውን ክስተት ለማጣራትና ተገቢውን እርምጃ ለመውሰድ እንዲሁም የታገቱ ህጻናትንም ለማስመለስ የፌደራል ፖሊስ ከክልሉ የጸጥታ ሃይል ጋር በመሆን በጋራ እየሰራ ይገኛል።

ከዚህ በፊት የጋምቤላ ክልል ከደቡብ ሱዳን ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች ከአጎራባቹ የሙርሌ ጎሳ ሰርገው በሚገቡ ታጣቂዎች ተመሳሳይ የህጻናት እገታና ጥቃት መፈጸሙ ይታወሳል።

የአካባቢውን ጸጥታ ለማስጠበቅ የሁለቱ ሃገራት አጎራባች ክልሎች አስተዳደርና የፌደራል ፖሊስ ችግሮችን ለመፍታት ባደረጉት ጥረት፥ በአካባቢው በታጣቂዎች ይፈጸሙ የነበሩ የሰረጎ ገብ ታጣቂዎችን እንቅስቃሴ ለመቀነስ ተችሎ ነበር።

አሁን የተፈጠረውን ክስተት በተመለከተም የታገቱትን አምስት ህጻናት ለማስመለስ ከሚደረገው ጥረት ባሻገር በሁለቱም ሃገራት አጎራባች አካባቢዎች የሚኖሩ የሃገር ሸማግሌዎችንና የማህበረሰቦቹን ተወካዮች ባሳተፈ መልኩ ዘላቂ ሰላምን በአካባቢው የማስፈን ጥረት ይቀጥላል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.