Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የግብርና ዘርፏን በማሳደግ በምግብ እህል ራሷን ለመቻል የምታደርገውን ጥረት እንደሚያግዙ የዓለም ባንክና የተመድ የስራ ሀላፊዎች ተናገሩ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የግብርና ዘርፏን በማሳደግ በምግብ እህል ራሷን ለመቻል የምታደርገውን ጥረት እንደሚያግዙ የዓለም ባንክና የተመድ የስራ ሀላፊዎች ተናገሩ።
በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተመራ ልዑክ በጅማ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች በክላስተር በመስኖ እየለማ የሚገኝ የስንዴ ማሳን፣ የቡና ልማትን እና ሌሎች የቱሪስት መስህቦችን ጎብኝቷል።
በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉት በምስራቅና ደቡብ አፍሪካ የዓለም ባንክ ዳይሬክተር ዑስማን ዲዮን እንደተናገሩት፥ በጉብኝታቸው አካባቢው ለግብርና እና ለቱሪዝም ዘርፍ ልማት ያለውን እምቅ አቅም መመልከት ችለዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፥ በአካባቢው እየተከናወነ ያለው የግብርና ስራ እና ለዘርፉ ያለው አመቺነት እንደዚሁም የቱሪዝም መስህብ የመሆን አቅም ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉ ናቸው።
ይህንን ከኦሮሚያ ክልል አልፎ ለኢትዮጵያ የመትረፍ አቅም ያለው ሀብትን የህዝብን ህይወት ለመለወጥ መዋል አለበት ያሉት ዳይሬክተሩ፥ የዓለም ባንክ ዋና ዓላማም እንዲህ ዓይነት ጥረቶችን መደገፍ ነው ብለዋል።
ይህም ጥረት እውን እንዲሆን ከክልሉ መንግስት እና በአጠቃላይ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ተቋማቸው እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
የተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ፀሃፊ ቬራ ሶንግዌ በበኩላቸው፥ በአካባቢው የሚመረተውን የግብርና ምርት ለገበያ ለማቅርብ ሆነ በኢኮ ቱሪዝም ሊለሙ የሚችሉት መስህቦች ጎብኚን እንዲጠሩ የመገናኛ አውታር እንደሚያስፈልግ ነው የገለፁት።
ተቋማቸው ባጠናው ጥናት መሰረት አፍሪካ ለመንገድ፣ ባቡርና ዓየር መሰረተ ልማቶች ማስፋፊያ 350 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ያስፈልጋታል።
ኢትዮጵያም በመንገድ ልማት መልካም ጅምር ላይ ናት ያሉት ዋና ፀሃፊዋ፥ በአየር ትራንስፖርት ልማት ደግሞ ጥሩ አፈፃፀም ያላት ሀገር መሆኗን አንስተዋል።
በመሆኑም የግብርና ልማት ዘርፏ እንዲያድግና ሀገሪቱ በምግብ እህል ራሷን በመቻል እንድትበለፅግ ተቋማቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ሆነ የዓለም ባንክን የመሰሉ ተቋማት ለድጋፍ ዝግጁ ሆነው እንደሚገኙ ነው የጠቆሙት።
በአልአዛር ታደለ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.