Fana: At a Speed of Life!

የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን በሚያዋስነው አካባቢ የተነሳውን እሳት ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን በሚያዋስነው አካባቢ የተነሳውን የእሳት ቃጠሎ የከፋ ጉዳት ሳያስከትል ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን በኦሮሚያ ደንና ዱር አራዊት የባሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ሥራ አስኪያጅ ተወካይ አቶ ቀነአ ዲዳ ለኢዜአ እንደገለጹት ፥ ከሁለት ቀናት በፊት የተነሳው የእሳት ቃጠሎ በባሌ ዞን በርበሬ ወረዳ ውስጥ ልዩ ስሙ ” በስመና ኦዶቡሉ” አካባቢ ነው፡፡

በሕገ ወጥ ከሰል አክሳዮች፣ ማር ቆራጮችና ለእንስሳት የግጦሽ ሳር እንዲበቅል እሳት በሚለኩሱ ግለሰቦች ቃጠሎ በተደጋጋሚ እንደሚከሰት አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት የተነሳው እሳትም መንስኤው እየተጣራ ቢሆንም ÷ ከድርቁ ጋር ተያይዞ ለእንስሶቻቸው መኖ ፍለጋ ወደ ደኑ ይዞታ የገቡ ግለሰቦች ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገመታል ሲሉ ነው አቶ ቀናአ የጠቆሙት፡፡

ከቦታው አስቸጋሪነትና አሁን ካለው ደረቅ የአየር ፀባይ ጋር ተያይዞ እሳቱን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ አድርጎታል ብለዋል፡፡

ቃጠሎ ከበርበሬ ወደ ጎባ ወረዳ እየሰፋ በመሆኑ በየደረጃው የሚገኙ የአስተዳደር፣ የጸጥታ አካላትና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ የከፋ ጉዳት ሳያስከትል ለመቆጣጠር የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

የተከሰተው የእሳት ቃጠሎ ወደ ዋናው የፓርኩ ጥቅጥቅ ደን ሳይዛመት ለመከላከል የአካባቢውን ማህበረሰብ በማሳተፍ እየተሰራ መሆኑን ያረጋገጡት ደግሞ የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ኃላፊ አቶ ሻሚል ከድር ናቸው፡፡

የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በብርቅዬ እንስሳትና ሌሎች ብዝሃ ህይወትን በማካተት በሀገሪቱ ለካርቦን ንግድ ሽያጭ የታጩ የተፈጥሮ ደኖች መገኛ በመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሻው ገልጸዋል፡፡

ቃጠሎውን ለመቆጣጠር እየተሳተፉ ከሚገኙ የበርበሬ ወረዳ አዋሽ ቆላቲ ቀበሌ ነዋሪዎች መካከል አቶ ኡስማን ሀሰን ፥ በህገ ወጦች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ሊጠናከር ይገባል ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

የኦሮሚያ ደንና ዱር አራዊት የባሌ ዞን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ከ542 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ የደን ይዞታ በስሩ ያስተዳድራል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.