Fana: At a Speed of Life!

በዞኑ በፀጥታ ችግር ምክንያት ሸሽተው የነበሩ ከ10 ሺህ በላይ የጉሙዝ ማህበረሰብ አባላት ወደ ቀያቸው ተመለሱ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በፀጥታ ችግር ምክንያት ሸሽተው የነበሩ ከ10 ሺህ በላይ የጉሙዝ ማህበረሰብ አባላት የአከባቢያቸው ሰላም በመስፈኑ ወደ ቀያቸው ተመለሱ።
 
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪው አቶ ጋሹ ዱጋዝ እንደገለጹት፥ እነዚህ ወገኖች ወደ ቀያቸው የተመለሱት የሀገር መከላከያ ሠራዊትና የፌደራል ፖሊስን ጨምሮ የፀጥታ ኃይሎች ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት በሰሩት ስራ የአካባቢው ሰላም በመመለሱ ነው።
 
የአካባቢው መረጋጋትን ተከትሎ ለህይወታቸው ሰግተው ወደ ጫካ ሸሽተው የነበሩት የጉሙዝ ማህበረሰብ አባላት ባለፉት ተከታታይ ሳምንታት ወደቀያቸው እንዲመለሱ መደረጉን ገልጸዋል።
 
በሰላማዊ መንገድ እጃቸውን መስጠት ያልፈለጉ ቀሪ የታጣቂውን ቡድን አባላት የማያዳግም እርምጃ የመውሰዱ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አቶ ጋሹ አስታውቀዋል።
 
በዞኑ የሚንቀሳቀሰው ታጣቂ የጥፋት ቡድን በአሁኑ ወቅት ከህዝብ እየተነጠለና አቅሙም በከፍተኛ ሁኔታ እየተዳከመ መምጣቱንም ገልጸዋል።
 
የክልሉ አደጋ ስጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን የመልሶ ማቋቋም እና አደጋ ምላሽ ዳይሬክተር አቶ አስረሳኸኝ አበጀ በበኩላቸው፥ ለተፈናቀሉ ወገኖች ሰብዓዊ ድጋፎችን ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
 
ዳይሬክተሩ አያይዘውም ተፈናቃዮችን በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም የረጅም ጊዜ ስትራቴጂክ ዕቅድ መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።
 
ስትራቴጂክ ዕቅዱ በቀጣይ አምስት ዓመታት የሚተገበር ሲሆን፥ ከ2 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ያስፈልጋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.