Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ ነገ በሚያካሂደው አስቸኳይ ስብሰባ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት ላይ ይወያያል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምክር ቤት ጉዳዮች አማካሪ ኮሚቴ በአራት አጀንዳዎች ላይ ከተወያየ በኋላ አጀንዳዎቹ ነገ በሚካሄደው የም/ቤቱ አስቸኳይ ጉባዔ እንዲቀርብ ወስኗል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጨምሮ፣ የመንገድ ትራንስፖርት ረቂቅ አዋጅን፣ የግል ሠራተኞች የጡረታ አዋጅ እንዲሁም የመንግስት ሠራተኞች አዋጅ የውሳኔ ሃሳብን ነው አማካሪ ኮሚቴው በአጀንዳነት የተወያየባቸው ።

አማካሪ ኮሚቴው በተለይም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አጀንዳ አስመልክቶ በስፋት የተወያየ ሲሆን፥ የአዋጁ መነሳት በአዋጁ መደንገግ አጋጥሞ የነበረውን ምጣኔ ሃብታዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ማሕበራዊ እንቅስቃሴዎች መቀዛቀዝ ለመፍታት ሚናው የጎላ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ እና የአማካሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ታገሰ ጫፎ አብራርተዋል ።

አዋጁ እንዲነሳ ሲታሰብ የሀገሪቷን የፀጥታ ስጋት ባገናዘበ መልኩ መታየቱንና ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮች በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሊፈቱ እንደሚችሉ ስለታመነበት መሆኑን አቶ ታገሰ ገልፀዋል ።

የአማካሪ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው፣ አሸባሪዎቹ ሕወኅት እና ሸኔ የፀጥታ ስጋት እንደሆኑ ናቸው፣ አዋጁ ከተነሳ ችግሩን ለመፍታት ምን ታስቧል ሲሉ ጠይቀዋል ።

የፀጥታ ስጋት ባለባቸው የአማራ፣ አፋር ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላና ወለጋ አካባቢዎች መንግስት የማስተካከያ እርምጃዎችን ለመውሰድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አቶ ታገሰ አብራርተዋል።

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሖመድ በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ እና ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክተው ለምክር ቤት አባላት ማብራሪያ እና ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እንደሚሰጡ አፈ-ጉባዔው ጠቁመዋል ።

የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በበኩላቸው፥ የሀገሪቷ የፀጥታ ሁኔታ በጥልቀት መገምገሙን ጠቅሰው፥ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች የተለየ ትኩረት እንደሚደረግ ተናግረዋል ።

ምክር ቤቱም ነገ በሚያካሂደው አንደኛ አስቸኳይ ስብሰባ በአዋጆቹ እና የውሳኔ ሃሳቦቹ ላይ ከተወያየ በኋላ ያፀድቃቸዋል ተብሎ ይጠበቃል ።

d

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.