Fana: At a Speed of Life!

የህወሓት ታጣቂዎች በአማራ ክልል ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጭካኔ የተሞላበት ግድያን ጨምሮ አስገድዶ መድፈርና ዘረፋ እንደፈጸሙ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ገለፀ፡፡

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የህወሓት ታጣቂዎች በአማራ ክልል ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጭካኔ የተሞላበት ግድያን ጨምሮ አስገድዶ መድፈርና ዘረፋ እንደፈጸሙ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ገለፀ፡፡

ተቋሙ ዛሬ ባወጣው ሪፖርት ነው በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሽብርተኛው ህወሓት ቡድን ግብረአበሮች ሰላመዊ ሰዎችን መግደላቸውን፣ በቡድን ሴቶችን መድፈራቸውን እና የግልና የህዝብ ንብረቶችን መዝረፋቸውን ያስታወቀው።

በጭና እና ቆቦ አከባቢዎች የተፈፀመው አረመኔያዊ ድርጊት በሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች እንደተፈጸመም ነው በሪፖርቱ የተመላከተው።

የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች ሊከተሏቸው የሚገቡትን መሰረታዊ የአለም አቀፍ የሰብዓዊ ህግ ደንቦችን ችላ ማለታቸውን የሚናገሩት በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ አፍሪካና እና ታላላቅ ሀይቆች አካባቢ ምክትል ዳይሬክተር ሳራ ጃክሰን ፥ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በሰው ልጆች ላይ አረመኔያዊ ድርጊትና የጦር ወንጀሎችን የሚያሳዩ መረጃዎች ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመሩ መጥተዋል።

በሆስፒታሎች ጭምር የተፈጸመውን የአስገድዶ መድፈር፣ የጅምላ ግድያ እና ዘረፋን እንደሚጨምር ምክትል ዳይሬክተሯ አንስተዋል።

በአማራ ክልል ሰሜናዊ ምስራቅ በምትገኘው የቆቦ ከተማ የትህነግ ወራሪ ያልታጠቁ ሰላማዊ ዜጎችን በአሰቃቂ ሁኔታ መግደላቸውን ያነሳው የአምነሲቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት፥ በአማራ የጸጥታ ሃይሎች እና አርሶ በአደሮች የደረሰበትን ሽንፈት ለመበቀል እንደሚሆን ገልጿል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስከሬን ለመሰብሰብ እና ለመቅበር የረዱትን ጨምሮ 27 ምስክሮች እና በህይወት የተረፉ ግለሰቦችን ቃለ መጠይቅ አድርጓል።

በዚህም 10 የቆቦ ነዋሪዎች ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል እንደተናገሩት ፥ ጳጉሜ 4 ቀን 2013 ዓ/ም ከሰዓት በኋላ የትህነግ ወራሪ ቡድን ዘመዶቻቸውን እና ጎረቤቶቻቸውን ከቤታቸው በማስወጣት ገድለዋል ።

ምስክሩ “መጀመሪያ ወንድሜን በጥይት ተኩሰው ገደሉት፤ ሌላኛው ወንድሜ እና የባለቤቴን ወንድም ለማምለጥ ሲሞክሩ ከኋላ በጥይት መትተው ገደሏቸው፤ በግራ ትከሻዬ ሲተኩሱብኝም የሞትኩ በማስመሰል እዚያው ወደቅኩ” ሲል ለአምነስቲ ኢንተርናሽናል አስረድቷል።

ሌሎች 12 የቆቦ ነዋሪዎች እንደተናገሩት፥ በአሸባሪው ቡድን የአካባቢው ነዋሪዎች እና የጉልበት ሰራተኞች አስከሬን ጭንቅላታቸው፣ ደረታቸው ወይም ጀርባቸው ላይ በጥይት ተመትተው እንዲሁም የተወሰኑት እጃቸውን ከኋላ ታስረው እንደተመለከቱ ለአምነሲቲ ኢንተርናስናል በሰጡት ቃል ገልጸዋል።

“የመጀመሪያው ሬሳ ያየነው በትምህርት ቤቱ አጥር ነው፤ በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ 20 አስከሬኖች የውስጥ ሱሪ ብቻ ያደረጉ ነበር።ብዙዎቹ የተተኮሰባቸው ጭንቅላታቸው ላይ ሲሆን ፥ የተወሰኑት ደግሞ ከኋላ ነው ፤ ከጭንቅላታቸው ጀርባ በጥይት የተመቱት ማንነታቸው ሊታወቅ አልቻለም” ሲሉ አንድ ነዋሪ ተናግረዋል።

በጭና የተፈጸመውን የአስገድዶ መድፈር የትህነግ ወራሪ ሃይሎች በ14 አመት እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሴቶችን እና ልጃገረዶችን ደፍረዋል ይላል።

ጾታዊ ጥቃቱም ድብደባ፣ የግድያ ዛቻ እና በማንነታቸው የሚደርስ ስድብን ጨምሮ በአሰቃቂ የጭካኔ ድርጊቶች የታገዘ ነበር።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያነጋገራቸው በህይወት የተረፉት 30 ሰዎች መካከል 14ቱ በበርካታ የወራሪው ቡድን ሃይሎች በቡድን እንደተደፈሩና የተወሰኑት ደግሞ በልጆቻቸው ፊት መደፈራቸውን በሪፖርቱ ገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪም የሽብር ቡድኑ በሁለቱም አካባቢዎች በርካታ የግል እና የህዝብ ንብረቶችን መዝረፉን በሪፖርቱ አውጥቷል።

ሳራ ጃክሰን፥ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እነዚህ አሰቃቂ ድርጊቶችን ለመመርመር፣ ተጠያቂ የሆኑትን ተጠያቂ ለማድረግ እንዲሁም በሕይወት የተረፉ ሰዎች መብቶቻቸውን ማስከበር እንዲችሉ አፋጣኝ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ አስታውቀዋል።

ሳራ ጃክሰን፥ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እነዚህ አሰቃቂ ድርጊቶችን ለመመርመር፣ ተጠያቂ የሆኑትን ተጠያቂ ለማድረግ እንዲሁም በሕይወት የተረፉ ሰዎች መብቶቻቸውን ማስከበር እንዲችሉ አፋጣኝ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.