Fana: At a Speed of Life!

ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ በማከናወንና አስፈላጊ የሰነድ ማሻሻያዎችን በማድረግ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንዲያስገቡ ምርጫ ቦርድ አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ በማከናወንና አስፈላጊ የሰነድ ማሻሻያዎችን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በማድረግ እንዲያስገቡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አሳሰበ፡፡

ምርጫ ቦርዱ ህዳር 23 ቀን 2014 ከፓርቲዎች ጋር ባደረገው ምክክር በአዋጅ ቁጥር 1162/11 እና በመመሪያ ቁጥር 3/2011 መሠረት ከ6ኛው አገራዊ ምርጫ መጠናቀቅ በኋላ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያካሂዱና የሰነድ ማሻሻያ እንዲያደርጉ የተገለፀላቸው ፓርቲዎች የሚጠበቅባቸውን አጠናቀው ባለማቅረባቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተነሳ በአንድ ወር ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን እንዲያከናውኑ እና ለቦርዱ እንዲያስገቡ መወሰኑ በምክክሩ ወቅትም ለፓርቲዎች መገለጹን አስታውሷል።

በዚህም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ መወሰኑን ተከትሎ ከስር ስማቸው የተዘረዘረ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባኤ በማከናወን እንዲሁም አስፈላጊ የሰነድ ማሻሻያዎችን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በማድረግ እንዲያስገቡ ምርጫ ቦርድ አሳስቧል።

አገራዊ ፓርቲዎችም ፥ የኦሮሞ ነፃነት ንቅናቄ፣ የኢትዮጵያ ነፃነት ፓርቲ ፣ የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ፣ ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ፣ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ፣ አዲስ ትውልድ ፓርቲ፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር፣ ብልፅግና ፓርቲ ፣ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ፣ ኅብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ናቸው፡፡

በተጨማሪም ክልላዊ ፓርቲዎች ፥ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ፣ ካፋ አረንጓዴ ፓርቲ፣ የጋምቤላ ሕዝብ ነፃነት ንቅናቄ፣ ሞቻ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ ኅዳሴ ፓርቲ፣ የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የአፋር ሕዝቦች ፍትሐዊ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ፣ ቦሮ ዴሞክራቲክ ፓርቲ፣ ዓረና ትግራይ ለዲሞክራሲ ሉዓላዊነት፣ የአርጎባ ብሔረሰብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ የአርጎባ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅትእና የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ መሆናቸውን ምርጫ ቦርድ አስታውቋል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.