Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለች – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር በመተባበር በቀጠናው ያለውን የሰላምና ፀጥታ ችግር በመቅረፍ ኢኮኖሚያዊ ትብብሯን አጠናክራ እንደምትቀጥል በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጎረቤት ሀገራትና የኢጋድ ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍስሐ ሻውል ገለጹ።

ከኤርትራ ጋር ከሦስት ዓመታት በፊት የተጀመረው የሰላም ስምምነት ከፍተኛ ዋጋ እንዳለው አምባሳደር ፍስሐ ሻውል ተናግረዋል።

አምባሳደሩ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት ፥ ከኤርትራ ጋር ሰላም ባይፈጠር ኖሮ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ የከፋ ሊሆን ይችል እንደነበር ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ከጂቡቲ ጋር ያላት ግንኙነትም በኢኮኖሚ፣ በህዝብ ለህዝብና በጠንካራ የአመራር ግንኙነት የቀጠለ መሆኑን አብራርተዋል።

ሶማሊያ እንደ ሀገር እንድትቀጥል የኢትዮጵያ አበርክቶ ጉልህ መሆኑን ያነሱት አምባሳደሩ ፥ የሁለትዮሽ ትብብሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ከኬንያ ጋር በፖለቲካና በፀጥታ መልካም ግንኙነት መኖሩን በማንሳት በኢኮኖሚውም ጠንካራ ግንኙነት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ለዚህም የላሙ ወደብ፣ የሞያሌ የአንድ ማዕከል የመተላለፊያ ኮሪደር መከፈቱን ገልጸው፥ ነጻ የንግድ ቀጠና ለመጀመርም በጥረት ላይ ነን ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከሌላኛዋ ጎረቤቷ ደቡብ ሱዳን ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንዳላት ያነሱት አምባሳደር ፍስሐ፥ በፈረንጆቹ 2018 የተደረሰው የሀገሪቱ የሰላም ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን ኢትዮጵያ የበኩሏን ጥረት እያደረገች ነው ብለዋል።

በአጎራባች አካባቢዎች የፀረ ሰላም ኃይሎችን እንቅስቃሴ ለመግታትም በጋራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የሱዳን ጉዳይ በተለየ ሁኔታ እንደሚታይ ገልጸው፥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሱዳኖች በኩል ለውይይት የሚጋብዙ አዝማሚያዎች መታየታቸውን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ መልካም ጉርብትናዋን ለማስቀጠል የተፈጠሩ ችግሮች በዘላቂነት ያለፀጥታ ችግር እንዲፈቱ ሁልጊዜ ለውይይት ቅድሚያ ትሰጣለች ነው ያሉት።

አምባሳደር ፍስሐ አክለውም ፥ የምስራቅ አፍሪካ አካባቢ በየጊዜው የሰላምና ፀጥታ መደፍረስ እያስተናገደ መሆኑን ገልፀው፥ ይህም ለኢኮኖሚያዊ ትብብርና የጋራ ብልፅግና ፈተና መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም ለሰላምና ፀጥታ ችግሮች ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ በመስጠት ኢትዮጵያንና ጎረቤቶቿን የሚያስተሳስር ኢኮኖሚያዊ ፕሮጀክቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.