Fana: At a Speed of Life!

ህብረ-ብሔራዊነትና ዘላቂ ሰላም እንዲጠናከር ኃላፊነታችንን እንወጣለን – ወጣቶች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለማቃለል ከሚያደርጉት ጥረት ጎን ለጎን ህብረ-ብሔራዊነትና ዘላቂ ሰላም እንዲጠናከር ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ የሦስተኛ ዙር የተሰማሩ የብሔራዊ የበጎ ፍቃድ ሥራ ተሳታፊ ወጣቶች ተናገሩ።

የሰላም ሚኒስቴር ያሰማራቸው የሦስተኛ ዙር ብሔራዊ የበጎ ፍቃድ አገልጋይ ወጣቶች ከድሬዳዋ አስተዳደር አመራሮች ጋር በሚቀጥሉት 10 ወራት በሚያከናውኗቸው ተግባራት ላይ ዛሬ ተወያይተዋል፡፡

ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመጡትና የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን የሆኑት ወጣቶቹ በውይይት መድረኩ ላይ በሰጡት አስተያየት፥ የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ በሚከናወኑ ተግባራት ላይ የድርሻቸውን ለመወጣት በቁርጠኝነት እንቀሳቀሳለን ብለዋል።

ከሲዳማ ክልል የመጣው ወጣት ነጋሽ ቦኩ፥ እኛ ከመላው ሀገሪቱ የተሰባሰብን ወጣቶች ያለንን የርስ በርስ ግንኙነትና አብሮነት በማጠናከርና በመደጋገፍ ህብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን ለማጠናከር እንተጋለን ብሏል፡፡

ወጣት ታየች መርጋ በበኩሏ፥ በድሬዳዋ ከሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች የሚቀስሙትን የፍቅር፥ የመቻቻልና የመደጋገፍ እሴቶች ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ተባብሮ የማደግ ተግባር ለማዋል እንደምትሰራ ተናግራለች፡፡

በድሬዳዋ ቆይታችን አንዳችን የሌላችንን ባህል፣ ቋንቋ፣ ታሪክ፣ እሴት ከማወቅና ጠንካራ ትስስር ከመፍጠር በተጨማሪ በከተማው የሚታዩ የማህበራዊ ችግሮችን ለማቃለል በዕውቀታችንና በጉልበታችን ኃላፊነታችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል ያለው ደግሞ ወጣት ሙክታር አህመድ ነው፡፡

ወጣት አሳየ በሪሶ በበኩሉ፥ ለተደረገላቸው ደማቅ አቀባበል አመስግኖ ፤ በቆይታቸው የአረጋውያንን ቤቶች ከመገንባት፣ መጠገንና ማጽዳት በተጨማሪ፣ በችግኝ ተከላና እንክብካቤ ሥራ ለማከናወን መዘጋጀታቸውን ተናግሯል፡፡

አሁን ሀገራችን ካለችበት የለውጥ እንቅስቃሴ አኳያ ከወጣቱ በዚህ ዘመን የሚፈለገው በሁሉም መስክ ባለው እውቀት፥ በክህሎትና ጉልበት ሀገርን ማሳደግ፣ ሰላምና ልማት ማረጋገጥ ነው ብሏል ወጣት አሳየ በሪሶ፡፡

በሰላም ሚኒስቴር የድሬዳዋ ብሔራዊ በጎ ፍቃድ አስተባባሪ አቶ ብሩክ መኮንን ፥ በመጀመሪያው ዙር በድሬዳዋ የተሰማሩ 98 የበጎ ፍቃድ አገልጋይ ወጣቶች በሰላምና ልማት ላይ በመሳተፍ 12 ሚሊየን ብር የሚገመትሥራ ማከናወናቸውን አስታውሰዋል።

ብሔራዊ የበጎ ፍቃድ ሥራው በውይይት የሚያምን፣ ለሀገር ልማትና ሰላም ምንጊዜም ዘብ የሚቆም አስተሳሰብን ማዳበር አስችሏል ብለዋል፡፡

በድሬዳዋ አስተዳደር የፍትህ፣ ፀጥታና የህግ ጉዳዮች ቢሮ የሰላም እሴት ግንባታ ዳይሬክተር አቶ ኢብሣ አሜ፥ የበጎ ፍቃድ አገልጋይ ወጣቶች ቀደም ሲል ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች አከናውነዋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በሁለተኛ ዙር በሥራ ላይ ያሉትንና አሁን በሦስተኛ ዙር የተመደቡትን በማቀናጀት የተሻለ ሥራ እንዲሰሩ ይደረጋል ነው ያሉት፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገበየሁ ጥላሁን ፥ ወጣቶቹ በቆይታቸው ስኬታማ ጊዜ እንዲያሳልፉና ውጤታማ ሥራ እንዲያከናውኑ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.