Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ስኬታማ ነበር- አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 10 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በመዲናችን የተካሄደው 35ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ስኬታማ እንደነበር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ፡፡
አምባሳደር ዲና ዛሬ ሳምንታዊ መግለጫ የሰጡ ሲሆን፥ አማርኛ ቋንቋን የአፍሪካ ኅብረት የስራ ቋንቋ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
አምባሳደር ዲና በመግለጫቸው በቅርቡ በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ስኬታማ እንደነበር ነው የገለጹት፡፡
ኅብረቱ የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከል ተቋምን ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ መወያየቱንም ተናግረዋል፡፡
የኮቪድ-19 ችግሮችና መፍትሄዎቸ፣ የሰላምና የጸጥታ ችግር፣ የመንግስት ለውጦቸ እና የመፈንቅለ መንግስት ጉዳዮች አሳሳቢ ሆነው መታየታቸውን ጠቁመው፥ የአፍሪካ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ሌላኛው አጀንዳ እንደነበር ገልጸዋል።
የአፍሪካ የፋይናንስና የእርስ በእርስ ንግድን ማጠናከር የሚለውም ጉዳይ ውይይት የተደረገበት አጀንዳ ነበር ብለዋል፡፡
አማርኛ ቋንቋን የአፍሪካ ኅብረት የስራ ቋንቋ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት አምባሳደር ዲና፥ ስዋሂሊኛ የኅብረቱ አንዱ የስራ ቋንቋ ሆኗል ብለዋል።
ኢትዮጵያዊቷ ሴት የኔፓድ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነው መመረጣቸው ትልቅ ስኬት መሆኑንም አመላክተዋል በመግለጫቸው፡፡

አምባሳደር ዲና በመግለጫቸው በኢትዮጵያ ሠላም፣ መግባባትና አንድነት ለመፍጠር አሸባሪው ህወሓት ከሽብርተኝነት መውጣት አለበት የሚሉ አካላት እንዳሉ ጠቁመው፥ ይህም በአገሪቷ የተከሰተው አለመግባባትና ግጭት በሠላማዊ መንገድ ይፈታል ብለው የሚያስቡ አካላት ፍላጎት እንጂ የኢትዮጵያ መንግስት አቋም አይደለም ብለዋል።

በሳዑዲ አረቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ ለተነሳው ጥያቄ አምባሳደር ዲና በሰጡት ምላሽ፥ በሳዑዲ የሚገኙ ዜጎቻችን አያያዛቸው እንዲሻሻል ምክክር እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፥ በሳዑዲ መንግስት በኩል የሚፈለገው ከአገር እንዲወጡ በመሆኑ ዋናው መፍትሄም ዜጎቻችን ወደ አገራቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ ማመቻቸት መሆኑን አመላክተዋል። የችግሩ ዋነኛ ምንጭ ህገ ወጥ ስደት መሆኑም ሊሰመርበት ይገባል ብለዋል።
የዜጎቻችን መሰደድ መስኤ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ቢሆኑም ሌሎች ጉዳዮችም ለህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ምክንያት መናቸውን ጠቅሰዋል።
እንደ አገር ትልቅ ስራ መሰራት ያለበት ህገ ወጥ ስደትን እና የሰዎች ዝውውር ወንጀልን ማስቀረት የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ነው ብለዋል።
ሰላም እና ልማት የኢትዮጵያ ዋና አጀንዳዎች መሆናቸውን የገለጹት አምባሳደር ዲና፥ ሰላምን በሚመለከት የተጀመሩት ጥረቶችም ድርድሮች ሳይሆኑ ንግግሮች ናቸው ብለዋል።
ለሰላምና ለልማት የሚጋብዙ ጉዳየች እንደ ጫና እና አስጋዳጅ ሳይሆን እንደ መልካም አጋጣሚ ሊወሰዱ ይገባቸዋል ነው ያሉት። ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ማጥበብ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ እንደሆነም ነው የጠቆሙት።
የኢትዮጵያ አና የአሜሪካ ግንኙነትን በተመለከተም ከአስተዳደራዊ ክንፉ ጋር ያለው ግንኙነት ጥሩ መሻሻል እያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።
የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ወደአገራችን የመጡትም ቀጠናዊ ሰላምን በተመለከተ ከከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ጋር ውይይት ለማድረግ መሆኑን አምባሳደር ዲና አስረድተዋል።
በሌላ በኩል የተባበሩት መንግስታት ምክትል ዋና ፀሀፊ አሚና መሀመድ÷ በኢትዮጵያ ተገኝተው በጦርነቱና በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችን ተዘዋውረው መጎብኘታቸውን እና በችግረሩ የተጎዱ ዜጎችን ለመደገፍ ጥረት እንደሚያደርጉ መግለፃቸውን አውስተዋል።
ምክትል ዋና ፀሀፊዋ የኢትዮጵያ መንግስት ለሰላም እያደረገ ያለውን ጥረት ማድነቃቸውንም ገለጸዋል::
በወንደሰን አረጋኸኝ
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.