Fana: At a Speed of Life!

በድርቁ ምክንያት ከብቶቻችንን በዝቅተኛ ዋጋ እንድንሸጥ ተገደናል-የቦረና አርብቶ አደሮች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቦረና በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ከብቶቻቸውን በዝቅተኛ ዋጋ እየሸጡ መሆኑን የአካባቢው አርብቶ አደሮች ተናገሩ፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ቅኝት ባደረገበት የከብቶች መገበያያ ላሞችና በሬዎች ከ500 ብር ጀምሮ ሲሸጡ ተመልክቷል።

ከብቶቻቸውን ሲሸጡ ያገኘናቸው አርብቶ አደሮች አያሌ ከብቶች በድርቁ ምክንያት እየሞቱ መሆናቸውን ገልፀው፥ ቀሪዎቹን ለማትረፍ ወደ ገበያ ቢመጡም ዋጋው አነስተኛ መሆኑን ያስረዳሉ።

ከዚህ ቀደም እስከ 40 ሺህ ብር ይሸጡ የነበሩ ከብቶቻቸው በአሁኑ ገበያ 500፣ 800 እስከ 3 ሺህ ብር እየተሸጡ መሆኑን ይህም በገበያ የሚፈልጉትን ለመሸመት እንዳላስቻላቸው ተናግረዋል።

ከሩቅ አካባቢ የሚመጡ አርብቶ አደሮች ለሽያጭ የሚመጡ ከብቶች ስለሚደክሙባቸው መንገድ ላይ ጥለው ለመሄድ እንደሚገደዱ የተናገሩ ሲሆን ፥ችግራቸውን ለመፍታትም ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

በዱብሉቅ ወረዳ ገበያ ልማት ፅህፈት ቤት የገበያ ጥናት ባለሙያው ደሳለኝ አባይነህ፥ የድርቁ ሁኔታ እንስሳትን መጉዳቱ ዋጋቸው እንዲያሽቆለቁል ማድረጉን ጠቁመው፥ ሻጭና ገዢን ለማገናኘትም ሙከራዎች እየተደረጉ መሆኑን አንስተዋል።

በቦረና ዞን ንግድ ፅህፈት ቤት የገበያ መረጃና ማስታወቂያ አስተባባሪ ቀራርሳ ዴራ በበኩላቸው ፥ ችግሩን ለመቅረፍ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር ለማስተሳሰር ቢሞከርም ከሀረማያ ዩኒቨርስቲ ውጭ ሌሎች ዩኒቨርስቲዎች ጋር በጋራ መስራት ባለመቻሉ ውጤታማ አለመሆኑን ነው ያነሱት።

የገበያ ሁኔታውን ለማስተካከልም ችግሩን ለማሳየት እየተሰራ መሆኑን አቶ ቀራርሳ ተናግረዋል፡፡

በአፈወርቅ እያዩ እና ታሪኩ ለገሰ

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.