Fana: At a Speed of Life!

ለአሸባሪው ህውሓት በድብቅ ሊተላላፍ የነበረ 60 ጀሪካን ቤንዚን ተያዘ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለአሸባሪው ህውሓት በድብቅ ሊተላላፍ የነበረ 60 ጀሪካን ቤንዚን መያዙን የዱብቲ ወረዳ ፓሊስ አስታወቀ።
የዱብቲ ወረዳ ፓሊስ አዛዥ ምክትል ኮማንደር ሳሊህ ማሂስ እንደገለጹት÷ ከመደበኛ የወንጀል መከላከል ሥራ በተጓዳኝ የሽብር ቡድኑ የጥፋት ተላላኪዎች እንቅስቃሴን ለመከታተል እየተሰራ ነው።
በተለይ ከአሸባሪው ህወሓት እንቅስቃሴ አንጻር መውጫ እና መግቢያ ቦታዎችን በመለየት በሰርዶ፣ በሰሃና እና በሸኮይታ ቀበሌዎች ህብረተሰቡን ያሳተፈ የቁጥጥር ሥራ እየተሰራ መሆኑን ነው ለኢዜአ የገለጹት፡፡
በዚህም ትናንት ከቀኑ 7:00 ሰዓት በወረዳው ሸኮይታ ቀበሌ ውስጥ 60 ባለ 25 ሊትር ጀሪካን ቤንዚን በህብረተሰቡ ጥቆማ በፓሊስ መያዙን ተናግረዋል፡፡ የተያዘው ቤንዚን ከ1 ሺህ 500 ሊትር በላይ እንደሚገመትም ገልጸዋል፡፡
ቤንዚኑን ከሎግያ-ሠመራ ከተማ በመኪና ተጭኖ ጨለማን ተገን በማድረግ በቀበሌው ሰዋራ ቦታ ላይ በግመል ተጭኖ በያሎ ወረዳ በኩል ወደ ህወሓት ሽብር ቡድን ቀጠና ሊገባ የነበረ መሆኑንም ምክትል ኮማንደሩ አስታውቀዋል። ተጠርጣሪው ግለሰብ አብሮ በቁጥጥር ስር ውሎ ምርምራ እየተደረገበት መሆኑም ተመላክቷል፡፡
በተመሳሳይ በኤሌደአር ወረዳ ትናንት ከሰአት የህወሓት ሽብር ቡድን አባል እንደሆኑ የተጠረጠሩና ተደብቀው ሲጓዙ የተገኙ ዘጠኝ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የወረዳው ፓሊስ አስታውቋል።
የወረዳው ፓሊስ አዛዥ ኮማንደር መሀመድ ሰኢድ እንደገለጹት÷ ተጠርጣሪዎቹ በጀቡቲ በኩል አቋርጠው በኤሊደአር ወረዳ ማንዳ ቀበሌ ልዩ ስሙ ዳባ በተባለ አካባቢ ሽብር ቡድኑን ለመቀላቀል ተደብቀው ሲጓዙ በህብረተሰቡ ጥቆማ በፓሊስ ተይዘዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ በሀላባ ቁሊቶ ከተማ በህገ ወጥ መንገድ በግለሰብ ቤት የተከማቸ ከ6 ሺህ 500 ሊትር በላይ ቤንዚን መያዙን የከተማው አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት ፅህፈት ቤት ገልጿል፡፡
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ሎቢሶ እንደገለጹት÷ በከተማዋ ሰሞኑን የቤንዚን እጥረት የተከሰተ ለማስመሰል የሚደረጉ ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎች ተስተውለዋል።
ኃላፊው እንዳሉት ከኅብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ ግብረ-ሀይሉ ትናንት 9 ሰዓት ንግድ ፈቃድ በሌላቸው ሁለት ግለሰቦች መኖሪያ ቤት ባደረገው ድንገተኛ ፍተሻ የተከማቸ ከ6 ሺህ 500 ሊትር በላይ ቤንዚን መያዝ ችሏል።
ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ቤንዚን በመሸሸግ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ የሚሰሩ የነዳጅ ማደያዎችንና የግለሰቦችን መኖሪያ ቤቶች በመለየት የሚደረገው ድንገተኛ ፍተሻና ቁጥጥሩ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ነው የገለጹት።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.