Fana: At a Speed of Life!

በሶማሌ ክልል ለተከሰተው ድርቅ ምላሽ ለመስጠት የክልሉ መንግሥት ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ አድርጓል- ርዕሠ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሌ ክልል ለተከሰተው ድርቅ ምላሽ ለመስጠት የክልሉ መንግሥት ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን ርዕሠ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ አስታወቁ፡፡

የሶማሌ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዘመን፣ 1ኛ ዓመት፣ 2 መደበኛ ጉባዔ ዛሬ የጀመረ ሲሆን፥ ጉባዔውም በመጀመሪያ ቀን ውሎው ቃለ ጉባኤ በማፅደቅ፣ የሶማሌ ክልል ርዕሠ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ ያቀረቡትን የክልሉ መንግሥት የ6 ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ኣዳምጧል፡፡

ርዕሠ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው በክልሉ ስለተከሰተው የድርቅ ሁኔታ ያነሱ ሲሆን፥ የክልሉ መንግሥት ለድርቅ ስለሰጠው ምላሽም ገለጻ አድርገዋል።

በድርቅ የተጎዱ ሰዎችና የእንስሳት ህይወት ለመታደግ የክልሉ መንግስት ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ ድርቁን ለመቋቋም ወጪ ማድረጉንም ነው ያብራሩት፡፡

በክልሉ በተከሰተው የድርቅ አደጋ ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ምላሽ መሰጠቱን ጠቁመው፥ የሶማሌ ክልል መንግስት በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን በኩል ባቀረበው የወገን ደራሽ ጥሪ ተከትሎ የሀገራችን ከፍተኛ መሪዎች፣ የተመድ ከፍተኛ አመራሮች፣ የዩ ኤስ አይ ዲ አመራሮች፣ ክልሎችና የከተማ አስተዳደር አመራሮች እንዲሁም በርካታ የአለም አቀፍ ግብረሰናይ ድርጅቶች ወደ ክልሉ መጥተው የድርቁ ሁኔታና የክልሉ መንግሥት እያደረገ ያለውን ርብርብ ተመልክተዋል ብለዋ፡፡

ከተለያዩ የሀገራችን ክልሎች፣ ከግሉ ማህበረሰብ ከሀገር በቀል ለጋሽ ድርጅቶችና ከተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች በገንዘብና በአይነት 305 ሚሊየን ብር መገኘቱንና ለድርቁ ምላሽ መደረጉንም ጠቁመዋል።

 

በሌላ በኩል ከአለም ባንክ በሳምንቱ መጨረሻ 64 ነጥብ 4 ሚልየን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ መገኘቱን ጠቅሰው፥ ከዚህ ውስጥ 38 ሚልየን ዶላሩ እንደተለቀቀና ድርቁን ለመቋቋም የሚደረገው ትግል ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ርዕሠ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው አመላክተዋል፡፡

 

ገቢው በሚቀጥሉት ወራት ለድርቁ መልስ ለመስጠት የሚያስችል ገቢ መገኘቱንና በተደጋጋሚ የሚከሰተውን ድርቅ መፍትሔ ለማበጀት ይውላልም ነው ያሉት፡፡

በዚህም ርዕሠ መስተዳድር ሙስጠፌ ድጋፍ ላደረጉ ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ ድርጅቶች፣ ግለሰቦች ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የሶማሌ ክልል በድርቁ አደጋ ለተጎዱ ዜጎች የመጠጥ ውሃ በማቅረብ ረገድ እያደረገ ያለው ርብርብ አስመልክቶ፥ የክልሉ መንግሥት በ87 ወረዳዎች የሚገኙ 1 ሺህ 873 ቦታዎች በየቀኑ ውሃ እየተጓጓዘ መሆኑንና በድርቁ ለተጠቁ ከ2 ነጥብ 4 ሚሊየን ህዝብ በላይ ተጠቃሚ ማድረጉንም አብራርተዋል።

በሌላ በኩል የክልሉ የለውጥ መንግሥት፣ በሁሉም የመሰረተ ልማት ዘርፎች ማለትም በትምህርት፣ በጤና፣ ግብርና፣ በመንገዶች ተጨባጭ ለውጦች ማምጣቱን ጠቁመው፥ መንግስት የተለያዩ ስትራቴጅያዊ እቅዶች ነድፎ ስኬታማ ሥራዎች መስራቱንና እየተሰሩ መሆኑን መናገራቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የከተሞችን እድገት ከማሳደግ አኳያ ከተሞች በትራንስፖርትና በህዝብ አገልግሎት ለማስተሳሰር እንዲሁም የከተሞችን ደረጃ የሚያጎለብቱ ሥራዎች በተለይ በጅግጅጋና ጎዴ ከተሞች አሁናዊና ለወደፊትም ለውጥ የሚያመጡ የአስፋልትና ኮብልስቶን መንገዶችን መገንባታቸውንና አሁንም ሌሎች በርካታ መንገዶች እየተገነቡ መሆኑንም ርዕሠ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ በሪፖርታቸው አመላክተዋል፡፡

 

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.