Fana: At a Speed of Life!

አገልግሎቱ የህክምና መሳሪያዎችን ለአምደ ወርቅ ሆስፒታል ድጋፍ አደረገ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር የሚገመት የህክምና መሳሪያዎችን ለአምደ ወርቅ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ድጋፍ አደረገ።

በአሸባሪው ህወሓት ወራሪ ቡድን ጉዳት የደረሰበትን የዓምደወርቅ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታልን ሙሉ በሙሉ ወደስራ ለማስገባት የህክምና ቁሳቁስ እጥረት እንደነበረበት በኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት የስርጭትና ስምሪት ዳይሬክተሩ አቶ እንዳለው አስማማው ተናግረዋል።

ከተቋሙ ውስጥ ገቢ በመቀነስ ሆስፒታሉን በዘመናዊ የህክምና ቁሳቁሶች ለማደራጀትና ለታካሚዎች የተሟላ አገልግሎት ሆስፒታሉ መስጠት እንዲችል አይነታቸው 53 የሆኑ የህክምና መሳሪያዎችን በ1 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ወጪ ለሆስፒታሉ ድጋፍ ተደርጓል።

ድጋፉ በቂ ነው ብለን አናምንም ያሉት አቶ እንዳለው ፥ አሁን ያደረግነው ድጋፍ ከማህበረሰቡ ጎን መሆናችንን ለማረጋገጥ ነው።

የአምደወርቅ ሆስፒታል በህልውና ዘመቻው ከፍ ያለ መጠን መድሃኒት በተቋሙ ይቀርብለት እንደነበር ዳይሬክተሩ ገልፀው ፥ የተደረገው ድጋፍ ከሆስፒታሉ ፍላጎት መነሻ ነው ብለዋል ።

በቀጣይም በአማራና አፋር ክልሎች በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማት በህክምና ቁሳቁስ የማደራጀትና ድጋፍ የማድረጉ ተግባር አጠናክሮ ይቀጥላል ተብሏል።

የአምደወርቅ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ብርሃኑ አለሙ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለፁት ፥ አሸባሪው የትህነግ ወራሪ ሃይል በአምደወርቅ ከተማ በቆየባቸው ጊዜያት የሆስፒታሉን የህክምና ቁሳቁሶችን መዝረፉንና ማውደሙን ገልጸዋል።

በአጠቃላይ በወራሪ ሀይሉ ሆስፒታሉ 112 ሚሊየን 792 ብር የንብረት ውድመት እንደደረሰበት የተናገሩት ስራ አስኪያጁ ፥ አሁን የተደረገው ድጋፍ ሆስፒታሉ አቁሟቸው የነበሩ ህክምናዎችን አገልግሎት ለማስጀመር ዕድል ይፈጥራሉ ብለዋል።

ሆስፒታሉ ከአንድ ወር በፊት መደበኛ ስራውን እንደጀመረ የተገለጸ ሲሆን፥ የፋና ባልደረባ በስፍራው ተገኝቶ ሆስፒታሉ መደበኛ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አረጋግጧል።

በምናለ አየነው

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.