Fana: At a Speed of Life!

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት መጀመሩን አስመልክተው ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ምን አሉ ?

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዛሬ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨቱን አስመልክተው ሰፊ ሽፋን ሰጥተውታል።

ቢቢሲ፣ አልጀዚራ እና ፍራንስ 24፤ አህራም ኦንላይን ፣ ሲ ጂ ቲ ኤን ና ሮይተርስ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አወዛጋቢና የቢሊየን ዶላር ፕሮጀክት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የድል ጉዞ ጅማሮን በይፋ መመረቃቸውን ዘግበዋል፡፡

አልጀዚራ እና ፍራንስ 24 ÷ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የግድቡን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ጅማሮ ሲያበስሩ “ግድቡ በኢትዮጵያውያን የተገነባ ቢሆንም፥ ተጠቃሚ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ አፍሪካውያን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችንም ጭምር ናቸው ማለታቸውንም ጠቅሰዋል።

“ኢትዮጵያ ኃይል ማመንጨት ጀመረች” በሚል ርዕስ የጻፈው ቢቢሲ ፥ ኢትዮጵያ ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ከዓባይ ወንዝ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት ስራዋን ጀመረች ሲል ዘግቧል።

ቢቢሲ እንደዘገበው ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ከምትገነባው ግድብ የሚመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ለልማት ሥራዎቼ እጅግ ያስፈልገኛል የሚል ጽኑ አቋም ያላት ቢሆንም፥ ግድቡ በኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ መካከል አወዛጋቢ ሆኖ መቆየቱን ገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግስት በድርቅና በጦርነት የተጎዳውን የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለመለወጥ የግድቡ ግንባታ ወሳኝ ሚና እንዳለውና በታችኛው የተፋሰሱ አገሮች ላይ ጥቅም እንጂ የሚያስከትለው ጉዳት እንደሌለ ሲገልጽ መቀየቱንም ዘገባዎቹ አመላክተዋል።

ግብፅ እና ሱዳን ግን በዓባይ ውሃ ላይ ጥገኛ በመሆናቸው ግድቡን አሁንም እንደ ስጋት እየተመለከቱት መሆኑን አንስተዋል፡፡

የዜና ምንጮቹ የ4 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላሩ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ቀድሞ ኢትዮጵያውያን ሲያገኙ የነበረውን የኤሌክትሪክ ኃይል በእጥፍ እንደሚያሳድግ ገልጸዋል።

የግድቡ ግንባታ ሲጠናቀቅ ከ5 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳለውም ነው የጠቀሱት።

የመንግስት ሠራተኞችን ጨምሮ መላው የኢትዮጵያ ዜጎች ቦንድ በመግዛት እና በማዋጣት ፕሮጀክቱን እውን ማድረጋቸውንም አልጀዚራ በዘገባው አትቷል፡፡

በአሁኑ ጊዜም በአንዱ ተርባይን ብቻ 375 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት መጀመሩም በዜና አውታሮቹ ተዘግቧል፡፡

ፍራንስ 24 ÷ ግብጽ በፈረንጆቹ 1929 የተደረገውን የቆየ ስምምነት በማንሳት በዓባይ ላይ ታሪካዊ የባለቤትነት ጥያቄ እንዳላትና 100 ሚሊየን ግብጻውያን በዓባይ ወንዝ ላይ የተመሠረተ ሕይወት እንደሚመሩ ብሎም በወንዙ ላይ የሚከናወነው ግንባታ የውሃ ፍሰቱን ይቀንሰዋል በሚል ሰበብ ከፍተኛ ጭንቀት እንደፈጠረባቸው ጠቁሟል፡፡

አህራም ኦንላይን በበኩሉ ÷ ግብጽና ሱዳን የግድቡን ግንባታ እንዳልተቃወሙ ገልጾ፣ በአሞላሉ ላይ ግን ላለፉት አሥርት ዓመታት ሲመክሩ እንደቆዩና ኢትዮጵያ ከሀገራቱ የቀረበላትን አስገዳጅ የውል ሠነድ እንዳልፈረመች አውስቷል፡፡

ኢትዮጵያ ግብጽንም ሆነ ሱዳንን የሚጎዳ ምንም ዓይነት መጥለቅለቅም ሆነ ተፈጥሯዊ ያልሆነ የውሃ ፍሰት መገደብ አላደርግም ማለቷን አህራም ኦንላይን በዘገባው አመልክቷል፡፡

አፍሪካ ኒውስ በበኩሉ ÷ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በፈረንጆቹ 2024 ሲጠናቀቅ በአፍሪካ ትልቁ የውሃ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ እንደሚሆን ዘግቧል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ፕሮጀክቱ በጨለማ ውስጥ ለሚኖሩት ለአገሬ ዜጎች ብርሃን ለመስጠትና ለሀገሬ ልማት እጅግ አስፈላጊ ነው በማለት የግድቡ የውሃ ሙሌት እንዲቀጥልና በዛሬው ዕለትም ኃይል እንዲያመነጭ ማድረጋቸውን በስፋት አንስተዋል።

ሮይተርስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጠቅሶ እንደዘገበው ÷ የኢትዮጵያ ፍላጎት ለዕለታዊ የኃይል አቅርቦት ፍላጎታቸው የማገዶ እንጨት በጀርባቸው እየተሸከሙ ለሚሰቃዩ እናቶች ኃይል በማቅረብ ማሳረፍ መሆኑን እና 60 በመቶ ለሚሆኑት በጨለማ ውስጥ ለሚኖሩ ዜጎች ብርሃን መስጠት መሆኑን ጠቁሟል፡፡

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ሦስቱ ሀገራት በ2015 የፈረሙት “ማንኛውም ሀገር ያለሌላው እውቅና በውሃው ላይ ምንም ማድረግ አይችልም” የሚለውን ስምምነት ኢትዮጵያ ጥሳለች በማለት ስሞታ እንዳሰሙም ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

የቻይናው ሲቲጂ ኤን በበኩሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የግድቡ ኃይል የማመንጨት ሰራ መርቀው እንዳስጀመሩ ገልጾ፥ “እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ዋጋ የከፈለለት፥ ተስፋ ያደረገበትና የፀለየለት ሥራ በስተመጨረሻ እዚህ ደረሰ “ ማለታችውን ጠቅሶ ዘግቧል።

“ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ” የሚል ስያሜ የሚታወቀው የኢትዮጵያ ግድብ፥ እስካሁን በአፍሪካ ትልቁ ግድብ ነው ሲሉም መገናኛ ብዙሃኑ ዘግበዋል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.