Fana: At a Speed of Life!

ለህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ በስኬት መጠናቀቅ የላቀ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት የእዉቅናና የምስጋና መርሃ-ግብር ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ህብረት 40ኛው የመሪዎች ጉባኤ እና የ35ኛው የስራ አስፈጻሚ ም/ቤት ስብሰባ በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላደረጉ የባለድርሻ አካላት የእውቅና እና የምስጋና መርሃ-ግብር ተካሄዷል።
 
በስነ-ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን መርሐ ግብሩ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሃይል ማመንጨት በጀመረበት ማግስት የተካሄደ በመሆኑ ድርብ ደስታ ይሰጣል ብለዋል።
 
አክለው ጉባኤውን ኢትዮጵያ ለማስተናገድ የገባችዉን አደራ በትብብር እና በአንድነት መንፈስ በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ሌት ከቀን በመስራት ዉጤታማ እንዲሆን ላደረጉ ባለድርሻ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
 
አቶ ደመቀ መኮንን፥ ጉባኤው በተሳካ ሁኔታ እንዳስተናገድን ሁሉ በሌሎች መስኮች በትብብር በመስራት ውጤት ማስመዝገብ ይጠበቅብናል ብለዋል።
 
እንዲሁም ሌሎች መሰል ትላልቅ ስብሰባዎችን ለማስተናገድ የአሁኑ ተምሳሌታዊ ተሞክሮ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል
 
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በበኩላቸው በተቀናጀ ሁኔታ ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ በትብብር በመስራት በላቀ ስኬት እንዲጠናቀቅ ላደረጉ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የጸጥታ ተቋማት፣ የግል ተቋማት እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የስራ ባልደረቦች ምስጋና አቅርበዋል ።
 
በመጨረሻም አቶ ደመቀ ለጉባኤው መሳካት አስተዋጽኦ ላበረከቱት የባለድርሻ አካላት የምስጋና የምስክር ወርቀት ሰጥተዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.