Fana: At a Speed of Life!

በአሸባሪ ቡድኑ ውድመት የደረሰበት የኮምቦልቻ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ወደ አገልግሎት ተመለሠ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጉምሩክ ኮሚሽን የኮምቦልቻ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በጦርነቱ ከፍተኛ ዘረፋ እና ውድመት ከተፈጸመበት በኋላ አስፈላጊው ግብዓት ተሟልቶለት ከታኅሣሥ 18 ቀን 2014 ጀምሮ ወደ አገልግሎት መመለሱ ተገለጸ፡፡

18 ሚሊየን ብር የሚያወጡ ቅርንጫፉ ሲገለገልባቸው የነበሩ ቋሚ እቃዎች፣ ከ1 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ የቢሮ አላቂ እቃዎች፣ በኮንትሮባንድና በንግድ ማጭበርበር በቁጥጥር ስር ውለው በመንግስት መጋዘን ውስጥ በሞዴል 265 እና 270 የተቀመጡ እቃዎችን ለማስወገድ በጨረታ ሂደት ላይ የነበሩ እንዲሁም በህግ ክርክር ሂደት ላይ የነበሩ ንብረቶችን ጨምሮ በድምሩ 169 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር የሚገመቱ ንብረቶች በወራሪዉ ኃይል ተዘርፈዋል ፤ እንዲወድሙም ተደርገዋል ሲሉ የቅርንጫፉ የህግ ተገዥነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ከፍያለው ቢያዝን ገልፀዋል።

ምክትል ሥራ አስኪያጁ አክለውም በደረቅ ወደብ /ጊዜያዊ መጋዘን/ ውስጥ ገብተው የጉምሩክ ሥነ ስርዓት ያልጀመሩ ፣ የጉምሩክ ሥነ ስርዓት አጠናቀው በወደቡ የነበሩ ፣ የጉሙሩክ ሥርዓት ሳይፈጽሙ በደረቅ ወደብ የነበሩ እና የጉምሩክ ሥነ ስርዓት ለመፈጸም በሂደት ላይ የነበሩ የተለያዩ ግለሰብ አስመጪዎችና የመንግስት ተቋማት ንብረት የሆኑ እቃዎችን የያዙ በድምሩ 252 ኮንቴነሮች በወራሪው ጁንታ ኃይል ተወስደዋል ብለዋል።

ይሁን እንጂ በዚህ ምክንያት ሥራውን አቋርጦ የነበረው ጽሕፈት ቤቱ እንደገና መልሶ በማደራጀት አስፈላጊውን ግብዓት በሟሟላት ከታህሳስ 18/2014 ጀምሮ ሙሉ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ነው ያሉት።

አገልግሎቱን መስጠት ከጀመረ ጀምሮ በጥር ወር ብቻ ከብር 1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በቁጥጥር ሥር አውሏል፣ 151 ሚሊየን ብር ገቢም መሰብሰብ ተችሏል ሲሉም ገልፀዋል።

ህገ ወጥነትን በመከላከል የኅብረተሰቡን ደህንነት ለመጠበቅ በሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ምክትል ሥራ አስኪያጁ ጥሪ አቅርበዋል።

በአንድነት ናሁሰናይ

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.