Fana: At a Speed of Life!

በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ ሆኖም ኢኮኖሚው እድገት አስመዝግቧል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ ሆኖም ኢኮኖሚው እድገት አስመዝግቧል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለፁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ እና ምላሽ እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
በምላሻቸው በተለያዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ፈተናዎች ውስጥ ሆኖም ኢኮኖሚው እድገት አስመዝግቧል ነው ያሉት፡፡

በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት የተገኘው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ14 ነጥብ 9 በመቶ እድገት ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን በበጀት ዓመቱ ባለፉት ስድስት ወራት 297 ቢሊየን ብር ወጪ ተደርጓል፤ ይህም ባለፉት ስድስት ወራት ወጪ ከተደረገው የ39 በመቶ እድገት አሳይቷል ነው ያሉት በማብራሪያቸው ።

በስድስት ወራቱ ውስጥ የወጪ ንግድ 25 በመቶ አድጓል፤ ከዚህም ውስጥ የሸቀጥ ወጪ ንግድ 21 በመቶ፣ አገልግሎት 27 በመቶ፣ ኢንዱስትሪ 25 በመቶ አድገዋል ብለዋል።

በአጠቃላይ ለ2 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የቀረበ ገቢ ከወጪ ንግዱ ተገኝቷል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡

በሌላ በኩል የገቢ ንግዱ 25 በመቶ ማደጉን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ለዚህም የምግብ ሸቀጥ፣ የነዳጅ እና የማዳበሪያ ዋጋ ማደግ ለገቢ ንግዱ መጨመር አስተዋፅኦ ማበርክቱን አመላክተዋል፡፡

በግማሽ ዓመቱ ውስጥ 1 ነጥብ 6 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንትን ሀገሪቱ ማግኘት ችላለች ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ23 በመቶ እድገት እንዳለው ነው ያነሱት፡፡

የዋጋ ግሽበት የሀገሪቱ ፈተና ሆኖ ቀጥሏል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በተለይም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ለምሳሌ ነዳጅ በዓለም ገበያ ላይ 85 በመቶ፣ የማዳበሪያ ዋጋ 176 በመቶ፣ የፓልም ዘይት 60 በመቶ፣ ስኳር 35 በመቶ እና ብረት 65 በመቶ መጨመሩን አስረድተዋል። ይህ ሁኔታ ግሽበትን ወደ ሀገር ውስጥ አምጥቷል ነው ያሉት በምላሻቸው።

የነዳጅ ዋጋን በተመለከተ በኢትዮጵያ መንግስት የሚደጎም በመሆኑ ከሁሉም የጎረቤት ሀገራት ዝቅ ባለ ዋጋ እየተሸጠ ነው፤ ይህም በመሆኑ በህገወጥ ነጋዴዎች በኩል ኢትዮጵያ ነዳጅን ለጎረቤት ሀገራት የምትልክ ሀገርም ሆናለች። ይህን ህገወጥ ድርጊት ለማስቆም የፀጥታ አካላት በህገወጥ ተግባሩ የተሰማሩ ቦቴዎችንም ሆነ ነዳጃቸውን እንዲወርሱ ታዘዋል ብለዋል።

የነዳጅ አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ ግን በወጣው ማሻሻያ መሰረት ደሃው ተደጉሞ ሀብታሙ ደግሞ በዓለም ገበያ ዋጋ እንዲገዛ በማድረግ እንደሚስተካከል ነው የጠቆሙት።

1 ቢሊየን ዶላር የሚገመት ከውጭ ሲገባ የነበሩ አንዳንድ ምርቶችን በሃገር ውስጥ መተካት ተችሏል፤ በዚህም የቢራ ብቅል ሙሉ ለሙሉ በሃገር ውስጥ ምርት ተተክቷል ነው ያሉት፡፡

በፋይናንስ ዘርፍ ባለፉት ስድስት ወራት የባንኮች አጠቃላይ ሃብት 2 ትሪሊየን መድረሱን የገለፁ ሲሆን ÷ ከዚህ ውስጥ የአክሲዮን ባለቤቶች ሃብት ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው 150 ቢሊየን ብር ወደ 159 ቢሊየን ብር አድጓል፡፡

የባንክ ቅርንጫፎች ቁጥርም ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው 6 ሺህ 700 ወደ 7 ሺህ 400 አድጓል ብለዋል። ተቀማጭ ሃብትም ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው 1 ነጥብ 35 ትሪሊየን ብር ወደ 1 ነጥብ 5 ትሪሊየን ብር አድጓል ነው ያሉት።

የሀገር ውስጥና የውጭ እዳ መጠን ከሀገር ውስጥ ምርት እድገት አንፃር 58 በመቶ ከነበረበት ወደ 50 በመቶ ወርዷል። የውጭ ብድር እዳ አምና ከነበረበት 30 ነጥብ 6 በመቶ ወደ 26 በመቶ ወርዷል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

የስራ እድልን በሚመለከት ዘርፉ በሚኒስቴር ደረጃ ከተቋቋመ በኋላ ሰፊ ስራ ተሰርቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥም ለ700 ሺህ ሰዎች የስራ እድል መፍጠር ተችሏል ብለዋል።
ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በአጠቃላይ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዘርፍ ላይ ለተገኘው ድል ከፍትኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል ነው ያሉት።
በሌላ በኩል በዘንድሮ በጋ ወቅት 600 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ ዘር መሸፈኑን ገልፀው በዚህም 25 ሚሊየን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ አመላክተዋል፡፡

የኩታ ገጠም ሜካናይዝድ አስተራረስ ምርታማነት እና ትርፋማነትን ስለሚያስገኝ አርሶ አደሮቻችን በስፋት ሊተገብሩት ያስፈልጋል ነው ያሉት በማብራሪያቸው።

በፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.