Fana: At a Speed of Life!

በቆሰሉ ታሪኮቻችን እና በምንገነባው ነገ ላይ የጋራ ውይይት ያስፈልጋል- ጠ/ሚ ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቆሰሉ ታሪኮቻችን እና በምንገነባው ነገ ላይ የጋራ ብሄራዊ ውይይት ያስፈልጋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዛሬ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛው አስቿኳይ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ስለብሄራዊ የምክክር ኮሚሽኑ አወቃቀር እና የአሰራር ሁኔታ በሰጡት ማብራሪያ፥ ሁሉንም ማህበረሰብ ለማቀራረብ መድረክ እና አጀንዳ መፍጠር ዋና ሥራው ይሆናል ብለዋል፡፡
የምንነጋገረው በቆሰሉ ታሪኮቻችን እና በምንገነባው ነገ ላይ ነው፤ የምንገነባው ነገ ከፓርቲ በላይ መሆኑን በመገንዘብ ተቃዋሚዎችም የተደራጀ ጠቃሚ ሃሳብ ይዘው ዕድሉን በበጎ ሊያዩት ይገባል ብለዋል፡፡
የናይል ዲፕሎማሲን በተመለከተም ከግብጽና ሱዳን ወንድሞቻችን ጋር በትብብርና ድርድር መስራት እንፈልጋለንለ፤ የዓባይን ውሃ የማቆም ፍላጎት የለንም፤ ይህም ሰሞኑን በተግባር ታይቷል ብለዋል፡፡
የአምባሳደሮች ምደባ አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ በቅርቡ ለአምባሳደሮች የተሰጠው ሹመት በተለያዩ መመዘኛዎች ላይ የተመረኮዘና ብቁ መሆናቸው የተረጋገጠ መሆኑን ገልጸው÷ አሁን ስልጠና በመውሰድ ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
ሳዑዲ አረቢያ ያሉ ኢትዮጵያውያንን በተመለከተም ከሳዑዲ መንግስት ጋር በቅርበት እየተሰራ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ÷ ከዚህ ጋር በተያያዘም ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ያለባቸውና የመንግስትን ድጋፍ የሚፈልጉ ወገኖች ያሉ መሆኑ የሚታመን ቢሆንም ለሃገር ጥፋት የሚሆኑ ሰዎችም አብረው እንዳይገቡ ለማድረግ በከፍተኛ ጥንቃቄ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ከአሸባሪው የህወሓት ቡድን ጋር በተያያዘ ከምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፥ እስካሁን ከህወሓት ጋር የተደረገ ድርድር አለመኖሩን አረጋግጠዋል፡፡
በእርስ በእርስ ጦርነት ፍጹም ድል ስለሌለ የሰላም አማራጭ ካለ እና ህወሓት ቀልብ ከገዛ ድርድር ማድረግ ክፋት እንደሌለውም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
አሸባሪውን የሸኔ ቡድን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያም፥ የወንጪ አካባቢን ልማት ያደናቀፈ፣ ዓላማና ኃላፊ የሌለው ጨካኝ ስብስብ መሆኑን ገልጸው፥ የኦሮሞን ልማት እያጠፋ ለኦሮሞ የቆምኩ ነኝ የማለት ሞራል እንደሌለውም አንስተዋል፡፡
የሚሽሎኮሎክ የሌባ ስብስብ እንጅ ፊትለፊት የሚገጥም ሃይል ባለመሆኑ፥ ሸኔ ለምን በህዝቡ ውስጥ ሊደበቅ እንደቻለ ከህዝቡ ውይይት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የክልል ልዩ ኃይል አወቃቀርን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፥ ኢትዮጵያ ስትጠቃ ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረጉን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡ አካሄዱን እና አወቃቀሩን በተመለከተም ስጋት በማይሆንበት ደረጃ አሰራር ሊበጅለትና ለሀገር በሚበጅ ሁኔታ ማደራጀት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ድርቅን በተመለከተ በሰጡት ምላሽ የዕለት ደራሽ ምግብ፣ አልሚ ምግቦች እና ክትባት በመድረሳቸው ሰዎች እንዳይሞቱ ማስቻሉን ጠቁመው፥ ከእንስሳት አኳያ ግን ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል ብለዋል፡፡
ለዚህም የረዥም ጊዜ መፍትሄው ውኃ አያያዝ፣ የገበያ ትስስር መፍጠር እና ደመናን ማዝነብን በስፋት ማስቀጠል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ በሰጡት ማብራሪያ እና ምላሽ የመንግስት ቀጣይ የአቅጣጫ ማዕቀፎችን ያስቀመጡ ሲሆን÷ በዚህም በሁሉም አግባቦች መከላከልን መሠረት ያደረገ አቅጣጫ መከተል፣ ምክክርን ማጠናከር፣ ዴሞክራሲን ማጠናከርና ማፅናት፣ ልማትና እድገትን እንዲሁም ብልጽግናን ማረጋገጥ እና ዲፕሎማሲን ማጠናከር መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘም ምክር ቤቱ ድጋፍ ካደረገልን በቀጣይ ስድስት ወራት የተሻለ ዕድገት ይመዘገባል ሲሉም ነው የገለጹት፡፡
በዮሐንስ ደርበው
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.