Fana: At a Speed of Life!

ሩስያ በኢትዮጵያ የብረት ፋብሪካ ለማቋቋምና ልምዷን ማካፈል እንደምትፈልግ ገለጸች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩስያ በዓለም ቀዳሚ ብረት አምራች ሀገር እንደሆነችና በኢትዮጵያ የብረት ፋብሪካ ለማቋቋምና ልምዷን ማካፈል እንደምትፈልግ ገለጸች።

በሩስያ የብረት ማዕድን ጉዳዮች ተወካይ በሆኑት ሰሜኖቭ ቪክተር የተመራው ልዑክ ከኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ሚኒስትር መላኩ አለበል ጋር በአዲስ አበባ ተወያይተዋል፡፡

ሩስያ በዓለም ቀዳሚ ብረት አምራች ሀገር እንደሆነችና ኢኮኖሚዋም በዋናነት የሚመራው በብረት ወጪ ንግድ እንደሆነች ሰሜኖቭ ቪክተር ተናግረዋል፡፡

ሩስያ በብረት ማዕድን ዘርፍ ላይ ዘርፉን የማሳደግ ብቃት ያላቸው በርካታ መሃንዲሶች እና የተማረ የሰው ኃይል እንዳላትና በኢትዮጵያም ብረት ፋብሪካ በማቋቋም ልምዷን ለማካፈል እንደምትፈልግም ገልጸዋል፡፡

አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው ÷ ኢትዮጵያ ዘላቂ ልማት እና የዴሞክራሲያዊ ባሕል እውን ለማድረግ ብሎም ከድህነት ለመላቀቅ የተቀናጀ ብሔራዊ ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ቀርጻ እየተገበረች መሆኑን ለልዑካኑ አስረድተዋል፡፡

በቀጣይም የግብርና መሩን ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር ባለመታከት እንሠራለን፤ አስቻይ ሁኔታዎችንም በመፍጠር የውጪውን ባለሀብት በሀገራችን መዋዕለ-ንዋዩን እንዲያፈስ እየሰራን ነውም ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ስትራቴጂ ሰፊ የገበያ አማራጭ ያላቸውን እና በከፍተኛ ደረጃ በጉልበቱ ሠርቶ መለወጥ የሚፈልገውን ዜጋ በግብዓትነት የሚጠቀሙትን ኢንዱስትሪዎች እንደሚያበረታታም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡

ኢንዱስትሪዎቹ የግብርና ምርቶችን እንደግብዓት በመጠቀም የሚያመርቷቸው ምርቶችም ለውጪ ገበያ እንደሚቀርቡና ከዚህ ቀደም ስናስገባቸው የነበሩ ምርቶችን እንደሚተኩም አቶ መላኩ አለበል አስረድተዋል፡፡

ሰሜኖቭ ቪክተር በበኩላቸው ኢትዮጵያ ወሳኝ ስትራቴጂካዊ ቦታ ላይ የምትገኝ በመሆኗ የወጪ ንግድን ለመሳብ ወርቃማ ዕድል ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን እና ዳር ድንበሯን ላለማስደፈር ባደረገቻቸው ትግሎች ሁሉ ሩሲያ ከጎናችን በመቆም የምንጊዜም አጋርነቷን አሳይታለች ያሉት አቶ መላኩ አለበል÷ አሸባሪው የህወሓት ቡድን በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ወረራ በፈጸመበት ወቅትም ሩስያ ሙሉ ድጋፏን በመስጠቷ የላቀ ምስጋና አቅርበዋል።

ሩስያ እና ኢትዮጵያ በወዳጅነት፣ በመተማመን እና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ታሪካዊ ትስስር ያላቸው ሀገራት እንደመሆናቸው መጠን በቀጣይም ሀገራችን ከሩስያ ጋር በትብብር የመስራት ፍላጎት እንዳላት መግለጻቸውን ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.