Fana: At a Speed of Life!

ጾሙ ምዕመናን ከጥላቻ፣ ፍትህን ከማጉደል፣ ከበደልና ዛቻ የሚቆጠቡበት ሊሆን ይገባል-ብጹዕ አቡነ ማቲያስ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 15፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በመጪው ወርሃ ጾም ምዕመናን ከጥላቻ ፣ ፍትህን ከማጉደል፣ ሰውን ከመበደልና ከዛቻ እንዲቆጠቡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አሳሰበች።

የቤተክርስቲያኗ ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ነገ በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚጀመረውን የአብይ ጾም አስመልክቶ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ፓትርያርኩ በመልዕክታቸው  ህዝበ ክርስቲያኑ ወርሃ ጾሙን ከቂምና ከበቀል ርቆ በመልካም ስነ ምግባርና በመንፈሳዊ ሕይወት አሸብርቆ ሊያሳልፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በዚህ ወቅት ማዳመጥ ያለብን የፈጣሪን ድምጽ ብቻ ነው ያሉት አቡነ ማትያስ፥የፈጣሪ ድምጽ ደግሞ ፍቅርና ሰላም፣ አንድነትና ስምምነት፣ እርቅና ይቅርታ ምሕረትና ቸርነት፣ ርሕራሔና ሀዘኔታ፣ ጸሎትና ምጽዋት፣ ፍትሕና እውነት እንዲሁም እኩልነትና ሕብረት ናቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያ አሁን የገጠማትን ችግር በጾምና በጸሎት ከመትጋት የተሻለ አማራጭ እንደሌለም ነው ያመለከቱት።

ጾም ሲባል ወደ ሰዎች አእምሮ የሚመጣው የእንስሳት ውጤት ከሆኑ ምግቦች መከልከልና ሰዓት ጠብቆ መመገብ መሆኑን ያነሱት አቡነ ማቲያስ ፥ ጾም በንስሐ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ መሆኑን መገንዘብ እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል።

ወደ ፈጣሪ ስንቀርብ በፍጹም ሐሳባችን፣ በፍጹም ልባችን በፍጹም ነፍሳችን ነውና በአካላችንና በመንፈሳችን ሁሉ ለእግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ ለመታዘዝ ዝግጁ በመሆን ነው  ሲሉም አስገንዝበዋል።

ምዕመናን ጾም ለእግዚአብሔር እንዲታዘዙ የሚያደርግ ፍቱን መሳሪያ በመሆኑ ወደ ፈጣሪ ቀርበው ለመለመንና ለመስማት እንዲሁም ንስሐ እንዲገቡ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ካቶሊካውያን ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት ብጹዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል ዓብይ ጾምን ምክንያት በማድረግ ለእምነቱ ተከታዮች ባስተላለፉት መልዕክት፥ወርሃ ጾሙን ለሀገር ሰላምና አንድነት ፈጣሪን በመማለድ ማሳለፍ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ጾም ለራስ ብቻ ከማሰብ ወጥተን በፈጣሪ ምሕረት ያገኘነውን የመንፈስ እርካታ ለሌሎች የምናስተላልፍበት የመቀራረብ፣ የመተሳሰብ፣ የመዋደድና እርስ በርስ በይቅርታ የምንጠያየቅበት ነው ሲሉ አመልክተዋል።

በጾም ወቅት ልግስናን በመፈጸም በተለያዩ ምክንያቶች ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን መርዳት እንደሚያሻ ካርዲናሉ ገልጸዋል።

ወቅቱ በተለይ የእግዚአብሔር ፍቅርና እንክብካቤ የሚያሻቸውን ድሆችን፣ በሕመም ምክንያት የሚሰቃዩትንና አረጋውያንን የምንጎበኝበት ሊሆን ይገባል ብለዋል።

ወላጆችም በዚሁ ወቅት ለልጆቻቸው መልካም ስነ-ምግባርን በማስተማር፣ በቤት ውስጥ የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ማበረታታት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.