Fana: At a Speed of Life!

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሰያ እና ዩክሬን በዓለም የምግብ ገበያ ውስጥ ቁልፍ ሚናን የሚጫወቱ ሀገራት መሆናቸው ይነገራል።

ዘ ኮንቨርሴሽን ባወጣው ፅሁፍ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች አሁን ላይ በሩሲያና ዩክሬን መካከል ለተከሰተው ግጭት ትኩረት ሊሰጡ ይግባል ይላል።

አሃዞች እንደሚጠቁሙት በሁለቱ ሀገራት እና በአፍሪካ መካከል ትርጉም ባለው መልኩ የግብርና ምርቶች ግብይት ይፈፀማል።

በአውሮፓውያኑ 2020 ላይ የአፍሪካ ሀገራት 4 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ የግብርና ምርትን ከሩሲያ ገዝተዋል። ከዚህ ውስጥ 90 በመቶ የሚሆነው ስንዴ ነው።

በዚሁ ተመሳሳይ ዓመት አፍሪካውያን ሀገራት 2 ነጥብ 9 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ የግብርና ምርት ከዩክሬን አስገብተዋል፤ ግማሽ የሚሆነው ስንዴ ሲሆን፥ 31 በመቶው ደግሞ የበቆሎ ምርት ነው።

በዋናነት ከእነዚህ ሀገራት የግብርና ምርቶችን በማስገባት ግብፅ ግንባር ቀደም ስትሆን፥  ሱዳን፣ ናይጄሪያ፣ ታንዛኒያ፣ አልጄሪያ ፣ ኬንያ እና ደቡብ አፍሪካ ይከተሏታል።

ሩሲያ እና ዩክሬን በዓለም የሸቀጦች ገበያ ውስጥ ትርጉም ያለው ድርሻ እንዳላቸው የሚነገር ሲሆን፥  ሩሲያ የዓለምን 10 በመቶ፣ ዩክሬን ደግሞ 4 በመቶ ስንዴን ያመርታሉ።

ሀገራቱ ምንም እንኳ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚያውሉት ምርት ቢኖርም በፈረንጆቹ 2020 ላይ ከዓለም የስንዴ ገበያ ውስጥ ሩሲያ የ18 በመቶ እና ዩክሬን የ8 በመቶ ድርሻ ነበራቸው።

ሀገራቱ በበቆሎ ምርት አቅርቦት ላይም ቢሆን ትርጉም ያለው ድርሻን ይዘዋል። ዩክሬን 40 በመቶውን የዓለምን የሱፍ አበባ ዘይትንም ታቀርባለች።

በመሆኑም አሁን ሩሲያ በዩክሬን የጀመረችው ወታደራዊ ዘመቻ እና ሀገራቱ ወደ ግጭት ውስጥ መግባታቸው በዓለም የምግብ አቅርቦትን እንደሚረብሸው ይታመናል።

የዚህ አሉታዊ ተፅእኖ በተለይም ከሁለቱ ሀገራት በስፋት የስንዴ እና የሱፍ አበባ ዘይት የምታስገባው የአፍሪካ አህጉር የግጭቱን አሉታዊ ተፅእኖ እንደትምቀምሰው ተገምቷል።

በተለይም አሁን ላይ በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት የተከሰተው  ድርቅ እና ረብሽ የገጠመው የዓለም የትራንስፖርት አገልግሎት ተደማምረው በአፍሪካ ቀድሞውኑ የከፋውን የምግብ ዋጋ ግሽበት እንዳያባብሰው ተሰግቷል።

ላለፉት ሁለት ዓመታት በቋሚነት እየጨመረ የመጣው የዓለም የምግብ ዋጋ በዚህ ግጭት መባባሱ እንደማይቀር እና በተለይም ለስንዴ ምርት በሁለቱ ሀገራት ላይ የተደገፉት የአፍሪካ ሀገራት የምግብ ዋጋ በአጭር ጉዜ ውስጥ አሁን ካለበት እንደሚንርባቸው ይግመታል።

እናም የአፍሪካ ሀገራት የሩሲያ-ዩክሬን ግጭት ጉዳይ ሊያሳስባቸው ይግባል ብሏል ፅሁፉ።

ካናዳ፣ አውስትራሊያና አሜሪካን የመሰሉ ዋነኛ ስንዴ አምራች ሀገራት በተፈጠረው ግጭት ምክንያት የተከፈተላቸውን  የገበያ እድል ተጠቅመው ምርታቸውን በገፍ ሊያቀርቡ እደሚችሉ ይገመታል። ሆኖም የሀገራት ዋነኛ ግብ ሊሆን የሚገባው በዓለም የምግብ ገበያ ውስጥ መሃል ተጫዋች የሆኑት ሩሲያ እና ዩክሬን ጠባቸውን አርግበው ግጭት እንዲቆም ማድረግ ሲል ፅሁፉ አብቅቷል።

 

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.