Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮ- ሶማሊያ አዋሳኝ ድንበር አካባቢዎች የፀጥታ ሁኔታን አስመልክቶ ውይይት ተደረገ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጁባላንድ ክልል የሰላም ሁኔታ እና በኢትዮጵያና ሶማሊያ አዋሳኝ ድንበር አካባቢዎች የፀጥታ ሁኔታ በተመለከተ ውይይት ተደረገ፡፡

በውይይቱ የጁባላንድ ክልል ፕሬዚዳንት፣ የሴክተር 3 አዛዥ፣ የሴክተር 6 አዛዥ፣ የ5ኛ ሞተራዝድ ዋና አዛዥና የጁባላንድ ክልል ፀጥታ ዘርፍ ሃላፊ እንዲሁም መረጃ ሃላፊ ተገኝተዋል፡፡

ውይይቱን የመሩት የጁባላንድ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አህመድ መዶቤ ፥ ኢትዮጵያና ሶማሊያ በታሪክ ፣ በባህል ፣ በቋንቋ የሚመሳሰሉ መሆናቸውን ጠቁመው ፥ ይህንን አንድነታችንን እና ወንድማማችነታችንን ለመሸርሸር አልሸባብ ሌት ተቀን እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

በመሆኑም አስከ ዶሎ ያሉትን ቦታዎች በመቆጣጠር በጋራ ሆነን ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

የሴክተር 3 አዛዥ ብ/ጄ ዘውዱ ሰጥአርጌ እንዳሉት ፥ በሶማሊያ የጠላት ሽብርተኝነት፣ የጎሳ ግጭት፣ የፌዴራልና የክልል መንግስት አለመግባባት ይሰተዋላል ፡፡

በህዝቡ ዘንድ መረጋጋት እንዳይኖር የሚሰሩትን አካላት በጋራ ሆነን በመለየት የሃገሪቱን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡

የሴክተር 6 አዛዥ ብ/ጄ አበባው ሰይድ በበኩላቸው ፥ የአሸባሪ ቡድኑን ሴራ ለማክሸፍ ከመስተዳድር አካላት፣ ከፀጥታ ሃይሉና ከህዝቡ ጋር በቅርበት በመገናኘት ችግሩን መፍታት ይገባል ብለዋል፡፡

የ5ኛ ሞተራይዝድ ሻለቃ ዋና አዛዥ ኮ/ል አሰፋ መኮንን ፥ “አሸባሪ ቡድኑ ጁባላንድንና ምዕራብ ሶማሊያን ለመቆጣጠር ያስባል፤ ሆኖም የአልሸባብን ተንኮልና ሴራ ቀድመን በመረዳት አንድ ዓይነት አረዳድ ይዘን አከርካሪውን መስበር አለብን” ሲሉ መናጋራቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.