Fana: At a Speed of Life!

የማርና ሰም ምርት ለማሳደግ 1 ሚሊየን ዘመናዊ ቀፎዎች ሊሰራጩ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የማርና ሰም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ 1ሚሊየን ዘመናዊ ቀፎዎችን ለማሰራጨት እየሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

በግብርና ሚኒስቴር የማርና ሐር ኃብት ዳይሬክተር አብርሃም ዘውዴ ለኢዜአ እንደገለጹት ፥ ኢትዮጵያ በዓመት እስከ 500 ሺህ ቶን ማርና 50 ሺህ ቶን ሰም ለማምረት የሚያስችል አቅም ያላት ቢሆንም እስካሁን ማምረት የቻለችው ከ15 በመቶ አይበልጥም ብለዋል።

“ካለን የንብ ቁጥር እና ተስማሚ የአየር ጸባይ አንጻር የማምረት አቅማችን ሙሉ በሙሉ አልተጠቀምንም” ይላሉ ዳይሬክተሩ ።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ፣ ከወቅታዊ ሁኔታ እና ከአርሶ አደሩ የግብይት ሰንሰለት ጋር ተያይዞ ወደ ውጭ የሚላከው የማር ምርት መጠን መቀነሱም ነው የተናገሩት።

የዘርፉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በስፋት አለመጠቀም፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የሚመረቱ ቀፎዎች ጥራት መጓደልና የአርሶአደሩ በቂ ክህሎት አለመኖርም ለምርቱ መቀነስ ምክንያት መሆናቸውን ገልጸዋል።

“ከዘርፉ ዋና ዋና ችግሮች መካከል የምንጠቀመው ባህላዊ ቀፎ ነው ፤ ቀፎውን ለመከታተል እና ማር ለመቁረጥ ምቹ አይደለም። በዚህም በኢትዮጵያ የማር ምርት ለማምረት 90 በመቶ ያህሉ ባህላዊ ቀፎ ተጠቃሚ ነው ሲሉም አንስተዋል፡፡

ምርታማነትን ለመጨመር ቀፎን የማዘመን ሥራና ለአረንጓዴ ልማት የሚተከሉ ችግኞችን ለንቦች ተስማሚ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች 1 ሚሊየን የሚደርሱ ዘመናዊ የሽግግር ቀፎዎች፣ ባለፍሬም ቀፎና ኢትዮ-ርብራብ ቀፎዎች በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ለማሰራጨት እየተሰራ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።

በማር ምርት የሰለጠኑ ወጣቶችን ወደ ሥራው እንዲገቡ የማድረግም ተግባር እንደሚከናወንም ተናግረዋል።

“ምርትና ምርታማነቱን ለማሳደግ ቀፎውን የማዘመን ሥራ እየሰራን ነው። አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ቀፎዎች ውስጥ ጫካ ላይ ተሰቅለው ነው ያሉት። ጫካ ላይ ተሰቅለው ካሉ ደግሞ ለተለያዩ ጠላቶች ይጋለጣሉ። ስለዚህ እሱን ወደ ምቹ ስፍራ ማድረግ ይገባል” ብለው ፥ “ጸሐይ ከነካው ሰሙን እንደሚቀልጥ ፣ ለንፋስ እንደሚጋለጡ እና ቅዝቃዜ ሲሆንም ሙቀታቸውን ለመጠበቅ ብዙ ሃይል ያወጣሉ። ሃይል አወጡ ማለት ደግሞ የማር ምርት ይባክናል“ ነው ያሉት፡፡

በዚህም ቀፎውን በማዘመንና 1 ሚሊየን ቀፎ በማሰራጨት ምርታማነትን ለማሳደግ መታቀዱ ተነስቷል።

በተጨማሪም በኦሮሚያ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያና በአማራ ክልል የእናት ንብ ማባዣና የሥልጠና ማዕከል ተገንብተው በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገቡም አስረድተዋል።

በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የማር ምርትን ማግኘት እንደሚቻል የጠቀሱት ዳይሬክተሩ ፥ በተለይም በኦሮሚያና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እምቅ አቅም ያላቸውና ዓመቱን ሙሉ ምርት የሚገኝባቸው ሥፍራዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ጎን ለጎንም ኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ የንብ ምርትን የማቀነባበርና ምርቱን ለአገር ውስጥና ለውጭ የሚያቀርቡ ፋብሪካዎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ከአሥር ዓመት በፊት አባል የሆነችበት የዓለም አቀፉ ንብ አናቢዎች ፌዴሬሽን /Apimondia/ የገበያ ትስስር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የሙያ ልውውጥ እንድታገኝ እገዛ ማድጉን ገልጸዋል።

የ2013 በጀት ዓመት የማር ምርት መጠን 129 ሺህ ቶን ሲሆን ፥ የሰም ምርት ደግሞ 6 ነጥብ 3 ሺህ ቶን እንደነበር ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

በኢትዮጵያ 1ነጥብ 8 ሚሊየን የሚሆኑ አርሶአደር፣ ከፊል አርብቶ አደር፣ ባለኃብቶችና የከተማ ነዋሪዎች የንብ ኤክስቴንሽን ምርት አናቢዎች ይገኛሉ።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.