Fana: At a Speed of Life!

126ኛው የአድዋ በዓል በካርኒቫል መልክ ይከበራል – ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) 126ኛው የአድዋ ድል በዓል አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች በካርኒቫል መልክ በየአውራ ጎዳናዎች እንደሚከበር የጥንታዊ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር አስታወቀ፡፡
የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ÷ ለ126ኛ ጊዜ የሚከበረውን የአድዋ ድል በዓልን በድምቀት ለማሳለፍ የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የአድዋ በዓል በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በጋምቤላ፣ በባህር ዳር፣ ድሬዳዋ እና የተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች ላይ እንደሚከበር የገለጹት ልጅ ዳንኤል÷ በዓሉንም በአግባቡ ያላከበረ ክልልም ሆነ የከተማ አስተዳደር በፌዴራል መንግሥት እንደሚጠየቅም አሳስበዋል።
የካቲት 23 ቀን 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባና በተለያዩ ከተሞች አውራጎዳናዎች ላይ በዓሉ በካርኒቫል መልክ እንደሚከበር ገልጸው÷ በዕለቱ የጥንታዊ ጀግኖች አርበኞችን የሚወክሉ አልባሳትንና ጌጣጌጦችን ያደረጉ ወጣቶች የተለያዩ ትርኢቶችን እንደሚያሳዩ ይጠበቃል፤ አጫጭር ተውኔትና፣ የመድረክ ላይ ትዕይንቶችም በበዓሉ ወቅት ለዕይታ ይቀርባሉ፤ የአገር ፍቅር ስሜት የሚያሰርጹ ሙዚቃዎችና ቀረርቶዎችም እንዲሁ በተመረጡ አደባባዮች ዪቀርቡ ይሆናል ብለዋል።
ነጋሪት የሚጎስሙና ዕምቢልታ የሚነፉ እንዲሁም በአገር ባህል ልብስ አጊጠው ከበሮ በመምታት ለበዓሉ ድምቀት የሚሰጡ ወጣቶች እንደሚሳተፉ ጠቁመው÷ በዓሉም በአገራዊ የአንድነት ስሜትና ባህላችንን በሚያስተዋውቅ መልኩ ለማክበር ዝግጅት መደረጉን ለኢፕድ ገልጸዋል።
ለበዓሉ ዝግጅት በፌዴራል ባህልና ስፖርት ሚኒስትር በኩል ዐቢይ ኮሚቴ መዋቀሩን ገልጸው÷ በኮሚቴው ውስጥ የተለያዩ የዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ለ126ኛው የአድዋ ድል በዓል የሚሆን ሎጎም ተዘጋጅቶ በመጽደቁ ለሕዝብ ይፋ ሆኗል። ቲሸርቶችና በዓሉን እንዲሁም የአገራዊ አንድነትን የሚፈጥሩ መልዕክቶች ያዘሉ አልባሳትም ለህብረተሰቡ ይቀርባሉ ብለዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እንዳስታወቀው÷ 126ኛው የአድዋ ድል በዓል “አድዋ ለኢትዮጵያውያን ኅብረት፤ ለአፍሪካ የነጻነት ጮራ” በሚል መሪ መልዕክት ይከበራል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.