Fana: At a Speed of Life!

ውስጣዊ ሰላምና አንድነትን በማጠናከር ማንኛውንም ጥቃት መመከት የሚያስችል አደረጃጀት መፍጠር ይገባል- አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ውስጣዊ ሰላምና አንድነትን በማጠናከር ማንኛውንም ጥቃት መመከት የሚያስችል አደረጃጀት መፍጠር ይገባል ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ተናገሩ፡፡
 
በሰሜን ወሎ ዞን ዳውንት ወረዳ በኅልውና ዘመቻው ለተፋለሙ ጀግኖች የእውቅናና የምስጋና መርሀ ግብር ተካሂዷል።
 
የወረዳው ሕዝብ ያለ በቂ መሣሪያ ጠላትን ፊት ለፊት የገጠመ ጀግና መሆኑ የተገለጸ ሲሆን÷ መስዋዕትነት ጭምር በመክፈል የአሸባሪውን ቡድን ከንቱ መሻት በተደጋጋሚ አክሽፎ ሽንፈት አከናንቦታል ተብሏል።
 
አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የኢትዮጵያን ኅልውና ለማስቀጠል የሕይወት መስዋዕትነት ለከፈሉ ጀግኖች ተገቢውን ክብር እንሰጣለን ነው ያሉት።
 
የአማራን ሕዝብ ከውርደት፤ ኢትዮጵያንም ከመፍረስ ለመታደግ ሲባል በተከፈለው መስዋዕትነት ጠላት አፍሯል ያሉት አቶ ገዱ÷ ጀግኖች በታሪክ ሲዘከሩ እንደሚኖሩ ገልጸዋል።
 
ይሁን እንጂ ትግሉ ገና አላለቀም፣ አሁንም ከፊት ለፊት ትግል እንደሚኖር ጠቅሰው÷ በተለይ በኢኮኖሚ መስክ ድህነትን መዋጋት ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ በአጽንኦት ተናግረዋል።
 
ውስጣዊ ሰላምና አንድነትን በማጠናከር ማንኛውንም ጥቃት መመከት የሚያስችል አደረጃጀት መፍጠር አስፈላጊ እንደሆነም መግለጻቸውን አሚኮ ዘግቧል።
 
የክልሉ መንግሥት በሁሉም አካባቢዎች የደረሱ ውድመቶችን መልሶ ለመገንባት እና የተጎጂ ቤተሰቦችን በዘላቂነት ለማቋቋም እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ፍስሃ ደሳለኝ ናቸው፡፡
 
የተጎጂ ቤተሰቦችን በዘላቂነት ተጠቃሚ ለማድረግ እና ጀግኖችን ለመዘከር ሁለገብ የገበያ አዳራሽ ለመገንባት ታቅዷል፣ ተግባራዊ እንቅስቃሴም ተጀምሯል ነው የተባለው።
 
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.