Fana: At a Speed of Life!

የሩሲያ-ዩክሬንን ጉዳይ በተመለከተ ቻይና ሁሌም ከሰላምና ፍትህ ጎን የምትቆም መሆኗን ገለጸች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ወቅታዊውን የሩሲያና ዩክሬን ጉዳይን በተመለከተ ቻይና ሁሌም ከሰላምና ፍትህ ጎን የምትቆም መሆኗን የአገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዋንግ ዌንቢን በተናገሩ፡፡
ቃል አቀባዩ በዛሬው እለት እንደተናገሩት፥ ቻይና በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ያለውን አለመግባባት ለማርገብ የሚያግዙ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን ሁሉ ትደግፋለች፤ ቀውሱ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታም ታግዛለች።
ቻይና በዩክሬን ጉዳይ ላይ ስላላት አቋም ስትጠየቅ መልሷ ሁሌም ከሰላም እና ፍትህ ጎን ትቆማለች የሚል መሆኑን ነው ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ላይ የተናገሩት።
 
ይህ በእንዲህ እንዳለ፥ የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በዩክሬን ጉዳይ ላይ ለመምከር ዛሬ ልዩ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲካሄድ ትናንት በድምጽ ብልጫ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።
 
ከ15 የፀጥታው ምክር ቤት አባላት 11ዱ የጠቅላላ ጉባኤውን መካሄድ ሲደግፉ፥ ሩስያ ተቃውማለች።
 
የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች፥ ህንድ እና ቻይና ደግሞ ድምጽ ሳይሰጡ ቀርተዋል።
 
የሩሲያ እና የዩክሬን የሰላም ውይይት አሁን በቤላሩስ በመካሄድ ላይ ሲሆን፥ ውይይቱ በቤላሩስና ዩክሬን ድንበር አካባቢ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
 
በሰላም ውይይቱ ላይ ለመሳተፍ የውጭ ጉዳይና ከመከላከያ ሚኒስቴር መ/ቤቶች እንዲሁም ከፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጽ/ ቤት የተውጣጣ የሩስያ የልዑካን ቡድን ቤላሩስ ዋና ከተማ ጎሜል የገባ ሲሆን፥ የዩክሬን ተወካዮችም በውይይቱ ላይ መሳተፋቸው ታውቋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.