Fana: At a Speed of Life!

ለአዲስ ተሿሚ አምባሳደሮች በዓለም የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሁኔታዎች ላይ ገለፃ ተደረገላቸው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአገሪቱን የኢኮኖሚ ልማት ዘርፍ ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የዓለም የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሁኔታዎችን ያማከለ ጠንካራ እና የማይበገር የኢኮኖሚ ስርዓት መገንባት እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ተናገሩ።

የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ለአዳዲስ ተሿሚ አምባሳደሮች ባደረጉት ገለፃ÷ አሁን ያለውን ዓለማዊ ሁኔታ በማጤን የአገራችንን ብሄራዊ ጥቅም ባስከበረ መልኩ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በስልጠናው የዛሬ ዉሎ “አገር በቀል ኢኮኖሚና የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ” በሚል ርዕስ ለተሿሚ አምባሳደሮቹ ገለፃ የተደረገላቸው መሆኑን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ዘርፈ ብዙ የሆነው የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስርዓት በሥራ እድል ፈጠራ ፣ በኢንቨስትመንት ፍሰት፣ የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ በመገንባት እና በዘላቂነት የማህበራዊ እድገት ለማምጣት እንደሚያስችል የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር እዮብ ተካልኝ ተናግረዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በታየው ዓለምአቀፍ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ሊደርሱ የነበሩ የኢኮኖሚ ስብራቶችን በመቋቋም እንዲሁም በአገራዊ የህልዉና ዘመቻው የጠላትን ፍላጎት በመቀልበስ እና የገጠሙ ፈተናዎችን በመቋቋም አሁን ላይ በአገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ላይ ውጤቶች መመዝገባቸዉን ዶክተር እዮብ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በአሁኑ ወቅት ኢኮኖሚውን የማነቃቃት ሥራ ይቀጥላል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው÷ የገቢ ማሰባሰብ አቅምን ማሳደግ፣ ምርታማነትንና የካፒታል ገበያን ማስፋፋት እና ፕራይቬታይዜሽን ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.