Fana: At a Speed of Life!

የዓድዋ ድልን በፍቅርና በወንድማማችነት ወደማይቀረው የጋራ ብልጽግናችን አብረን መጓዝ እንዳለብን ልንማርበት ይገባል- አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ 126ኛውን የዓድዋ ድል በዓልን በማስመልከት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
 
በመልዕክታቸውም የዓድዋ ድል በዓልን ጥላቻና መነቋቆርን አስወግደን በፍቅርና በወንድማማችነት ወደማይቀረው የጋራ ብልጽግናችን አብረን መጓዝ እንዳለብን ልንማርበት ይገባል ብለዋል፡፡
 
ርዕሰ መስተዳድሩ ያስተላለፉት ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
 
እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ከ 1884-1885 በጀርመን ዋና ከተማ በርሊን የተካሄደው አፍሪካን መቀራመትን ትኩረቱ ያደረገው የሴራ ኮንፈረንስ ለአፍሪካዊያን የጨለማና የታሪክ ጠባሳን ጥሎ አለፈ፡፡ ለአፍሪካውያን “ስልጣኔ” ያሻል በሚል ሽፋን ለዝርፍያ ያሰፈሰፉት ኢምፔራሊስቶች ቀደም ሲል ባስቀመጡት እቅድ መሰረት አፍሪካን እንደ ቅርጫ ስጋ ተቀራመ ቷት፡፡
 
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አፍሪካውያን ወይ ከማንነታቸው አሊያም ከሃብታቸው ሳይሆኑ ለክፍለ ዘመን በአስከፊ ባርነት ስር ተረግጠው ሲቆዩ ኢትዮጵያ ልጆቿ በከፈሉትት ውድ የህይወት መሰዋዕትነት ሉዓላዊነቷንና ክብሯን አስጠብቃ የዘለቀች ብቸኛ አፍሪካዊት ሀገር በመሆኗ ለወራሪዎች ድንጋጤና የሀፍረት ካባ በማልበስ በአንጻሩ ደግም ለአፍሪካዊያንና ለመላወ ጥቁር ህዝቦች የእኩልነትና ነጻነት ተምሳሌት አርማን በመትከል የማይደበዝዝ አኩሪ የጀግንነት ታሪክ አለም ላይ አስመዝግባለች፡፡
 
እውቁ የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ር ባህሩ ዘውዴ “ታይቶም ተሰምቶም በማይታወቅ ሁኔታ የጥቁር ጦር በነጭ ጦር ላይ ታላቅ ወታደራዊ ድል ተቀዳጀ” ብለው እንደ ገለፁት የአድዋ ድል የያኔውን የዓለም ፖለቲካ ትርክት የሻረ፣ የታሪክ ፍሰት አቅጣጫን በአዲስ የበየነ፤ የመላው ጥቁር ህዝቦች አኩሪ ድል ነው፡፡ ስለሆነም እኳን ለ 126ኛ የአድዋ ድል በዓል በሰላም አደረሳችሁ! ማለት እወዳለሁ፡፡
 
ታሪክ ዘሬ ላይ ቆመን የአሁኑ ማንነታችን መሰረት የሆነውን ትላንትን የምናይበት፤ አይተንም ለዛሬው ማህበራዊና ፖለቲካዊ መስተጋብራችን አዎንታዊ ትምህረት የምንቀስምበት እና ለነገው ማንነታችን ጠንካራ መሰረት የምንጥልበት መስታወት በመሆኑ ከአድዋ ድል ታሪክ ትውልድ ትልቅ ትምህረት ይወስዳል፡፡
 
የአውሮፓ ኢምፔራሊስቶች አፍሪካን የመቀራመት ሴራ ኢትዮጵያ ያከሸፈችበትና ብሎም ወራሪውነ ጣሊያን የውርደት ካባ ያከናነበችባት ትልቁ ሚስጢር የኢትዮጵያዊያን አንድነትና ጀግንነት ነው፡፡ ምንም እንኳ ውስጣዊ ችግርና አለመግባባት ቢኖር ሉአላዊነትንና ሀጋረዊ ክብርን በሚገዳደር ሀይል ላይ ኢትዮጲያዊያን ልዩነት ፈጠረው አያውቁም፡፡ የኦሮሞ ህዝብም የዚህ መልካም እሴት ባለቤት በመሆኑ፤ በኢትዮጲያ ሀገረ-መንግስት ግንባታ ታሪክ ውስጥ ከትላንት እስከ ዛሬ ለኢትዮጲያ ሉዓላዊነትና ኢትዮጲያዊ ማንነት ክብር ሲል ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር ሲዋደቅና መሰዋትነት ሲከፍል የዘለቀ ህዝብ ነው፡፡ በከፈለው የደም ዋጋና በከሰከሰው አጥንት የኢትዮጵያ ክብርና ሉአላዊነት ምሰሶ ሆኖ እየቀጠለም ነው፡፡
 
ወራሪው ጣልያንንና ሌሎች አውሮፓዊያን ኢምፔራሊስቶችን የውርደት ካባን ያከናነበ፣ እብሪታቸውን በማስተንፈስ በጥቁር ህዝቦችና በነጮች መካከል ምንም አይነት ሰብአዊ ልዩነት እንደሌለ ሚስጠር ሹክ ያለው የአድዋ ድል የኦሮሞ ጀግኖች ከወንድሞቻቸው ጋር ሆነው ከከፈሉት መሰዋትነት እና ካሳዩት ጀግንነት ውጭ እንዳልተሳካ ብዙ ፀሐፍት መስክረዋል፡፡ በመሆኑም የአድዋ ታሪክ ለጋራ ክብርና ሉኣላዊነት በወንድማማችነትና በጀግንነት አብሮ መቆምን፤ አብረው በክበር መሰዋትን ፤ ካንተ ሞት የኔ ሞት ይቅደም ተባብሎ ለሀገር ክብር ለሞት መሽቀዳደምን ያስተምረናል፡፡
 
ቀደምት አባቶቻችን ውስጣዊ ችግሮቻቸውን ቸል ብለው ጀግንነትን በተላበሰ ወንድማማችንት ለጋራ ክብርና ሀገራዊ ሉአላዊነት አብረው ለመቆም መወሰናቸው ዘሬ ነጻ ሀገር ሆነን ኩራት እንዲሰማን፤ አይበገሬና ኩሩ ህዝብ ተብለን እንድንታወቅ አድርጎናል፡፡ የዛሬውም ትውልድ ከዚህ መልካም የጀግነነትና አብሮ የመቆም እሴት ተቋዳሽ በመሆኑ በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት ከውስጥና ከውጭ ሀገርን የማፍረስ ሴራ በተሸረበብን ግዜ ልክ እንደ ትላነቱ በጋራ ቆመው ተላላኪውን ከነ ተልዕኮው በመቅበር ፤ላኪውንም አንገት በማስደፋት አይበገሬነታቸውን በማስመስከር የአድዋን ታሪክ መድገም ችለዋል፡፡ በመሆኑም፤ የኢትዮጲያን ክብርና ሉኣላዊነት የሚገዳደር ሀይል ካለ ዛሬም እንደ ትላንቱ እንደ እሳት ረመጥ የሚፋጅ እንደ አጋም እሾህ ጠላትን ፈታ የሚነሳ የአድዋ ጀግኖች ልጆች እንዳሉ ለውስጥ ጠላት ባንዳም ሆነ ለውጭ ሃይሎች ትልቅ ትምህረት አስተላልፏል፡፡
 
ይህ እንደ ተጠበቀ ሆኖ በአድዋ ላይ በሰራነው ደማቅ የጀግንነት ታሪክ የጥቁር ህዝቦች የድል ጎህ ፈንጣቂ ሆንን እንድንዘከር የረዳን ያ ጅግንነት፤ ያለምንም ልዩነት ባጋራ ተሰውቶ ለሃገር ክብር መስዋት መሆን፤ ከሞትህ ሞቴ ይቅደም ተባብሎ ለሃገር ክበር ለሞት የመሽቀዳደሙ እሴት እንደምን ለውስጣችን ችግሮች መፍትሔ መሆን ተሳነው የሚለው ጥያቄ ከሁላችንም መልስ የሚሻ አንገብጋቢ ጥያቄ ነው፡፡
ጥላንት በፍጹም ወንድማማችነት ስሜትና ጀግንነት ጠላትን አዋርደን ወደ መጣበት ለመመለስ ግዜ ያልፈጀን ህዝቦች፤ የሁላችንም ጠላትና የተጋላጭነታችን ምንጭ የሆነውን ድህነትን ተባብረን ማሰወገድ ላይ ዘመናትን እያስቆጠርን ነው፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው ደግሞ ከማይጠቅሙን ውል አልባና ጉንጭ አልፋ የፖለቲካ አጀንዳዎች ወጥተን በሚጠቅሙን ጉዳዮች ዙሪያ መግባባት ባለመቻላችን ነው፡፡ ምንም እንኳ ነፃነታችንን አስከብረን የኖርን ህዝቦች ብንሆንም፤ ድህነት እስካላ ድረስ ክብር የለምና ከአድዋ ታሪክ የወረስነውን የጀግንነት፣ የአብሮነትና የአንድነት እሴቶች የኢትዮጵያን ሁለንትናዊ ብልፅግናን በማረጋገጥ መድገም ይኖርብናል፡፡
 
ከአንድ ክፈል ዘመን በፊት የጥቁር ህዝቦች ሁሉ የነፃነት አርማን በአፍሪካ ምድር የተከለ፤ በተለይም ደግሞ ፓን አፈሪካኒዝምን የቀሰቀሰ ገድል የሰራ ህዝብ እንደምን ለወንድሙ የነጻነትና የሰላም ምንጭ መሆን ይሳነዋል? ሊያዋርደውና ነጻነቱን ሊነጥቅ የመጣበትን የውጭ ጠላት ለመመከት አብሮ መስዋዕትነትን የከፈል ህዝብ፤ መለስ ሲል እርስ በርሱ የሚገዳደል ከሆነ በአድዋ ድል የሰው ልጅ ሁሉ እኩልነትና ነጻ መሆኑን ያበሰርን ህዝቦች መባላችንስ ምኑ ጋር ነው? በከፈልነው መሰዋዕትነት ከስግብግብ ኢምፔራሊስቶች ዝርፍያ የጠበቅነውን የተፈጥሮ ሀብታችንን አልምተን የክብራችንና የብልዕግናችን ምንጭ ካላደረግነው፤ ቢያንስ ደግሞ ከተዘረፉት ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተሸለን ካልተገኘን የከፈለነው መሰዋዕትነት ትርጉሙ ምንድነው? የሚሉ የቁጭት ጥያቄዎች የአድዋን የድል በዓል እያከበርን ለቀጣዩ እጣፈንታችን ራዕይ የምንሰንቅበት መሆን አለበት፡፡
 
በመሆኑም፤ አድዋ ወንድማማችነት ነው፡፡ ጥላቻና መነቋቆርን አስወግደን በፍቅርና በወንድማማችነት ወደማይቀረው የጋራ ብልጽግናችን አበረን መጓዝ እንዳለብን ልንማርበት ይገባል፡፡ አድዋ ጀግንነት ነውና ይህ የጀግንነት እሴት የጋራ ጠላታችን የሆነውን ድህነትን በማስወገድ መደገም አለበት፡፡ አድዋ የነጻነትና እኩልነት አርማ ነውና አንዳችን ለሌሎቻችን የሰላም፤ የነጻነትና የእኩልነት ተምሳሌት በመሆን በመከባበር አብረን መኖር ይገባናል፡፡ ኢትዮጵያ በጋራ መልካም እሴቶቻችን የተገነባች ሀገር ናት፡፡የማይጠቅሙን ጥቂት ጉዳዮች ትተን በሚጠቅሙን በርካታ ጉዳዮች ላይ በማነጣጠር ወደ ምንናፍቀው ነገር ግን ወደማይቀረው የጋራ ብልጽግናችን በትብብር እንጓዝ፡፡
 
በድጋሚ እንኳን ለአድዋ የድል በዓል በሰላም አደረሰን!
 
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር
 
የካቲት 22/2014
 
ፊንፊኔ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.