Fana: At a Speed of Life!

የትምህርት ጥራት ችግርን ለመቅረፍ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ባለድርሻ አካላት መረባረብ አለባቸው ተባለ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው ከዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ካውንስል አባላትና መምህራን ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

በውይይቱ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ÷ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚስተዋለውን የትምህርት ጥራት ችግር ለመቅረፍ የተሻለ ሥርዓተ- ትምህርት መዘርጋት አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል።

ባለፉት አሥርት ዓመታት የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት መውደቁን የተናገሩት ሚኒስትሩ ÷ ጥራትን ያላማከለ የትምህርት ማስፋፊያና ተደራሽነት እንዲሁም የትምህርት እና የፖለቲካ ሥርዓት መጣመር ለውድቀቱ ምክንያት መሆናቸውን አንስተዋል።

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የዕውቀት ማበልጸጊያ ሆነው ሳለ ከተልዕኳቸው ውጪ የፖለቲካ አስተሳሰብ ማራመጃ መሆናቸው አግባብ እንዳልሆነም አውስተዋል።

ትውልዱ የሞራል ክስረት እንዳያጋጥመው ቤተሰብ ፣ የትምህርትና የሀይማኖት ተቋማት እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ርብርብ በማድረግ ማረቅ ይገባቸዋልም ነው ያሉት።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋን ለማፍራት ለትምህርት ጥራት ትኩረት መስጠት ይገባል ያሉት ሚኒስትሩ ÷ የትምህርት ሥርዓቱ ከታችኛው መዋቅር ጀምሮ ክፍተት ያለበት በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት ከሥርዓተ ትምህርት ቀረጻ ጀምሮ አስፈላጊውን ተሳትፎ በማድረግ ለትምህርት ጥራት መሻሻል ድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

በሚኒስትሩ የተመራው ልዑክ በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ ላቦራቶሪዎች እና ሰርቶ ማሳያዎችን ጎብኝቷል።

በማስተዋል አሰፋ

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.