Fana: At a Speed of Life!

”የሱዳኑ የመርሆዎች ስምምነት ተጥሷል” በሚል የግብጽ ሚዲያዎች የሚያናፍሱት ወሬ ሐሰት ነው – የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ”የሱዳኑ የመርሆዎች ስምምነት ተጥሷል” በሚል የግብጽ ሚዲያዎች የሚያናፍሱት ወሬ ሐሰት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፥ በኬኒያ፣ በህንድ እና በቤልጂየም የሚገኙት የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ከየሀገራቱ ተወካዮች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በዚህም በኢትዮጵያ ስላለው ነባራዊ ሁኔታ ለየሀገራቱ ለማስረዳት የተቻለ ሲሆን፥ ከሀገራቱ ጋር ያለው የንግድ፤ የኢንቨስትመንትና የፖለቲካ ግንኙነት በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይም ውይይት ተደርጓል ብለዋል።

በሀገር ውስጥ ደግሞ የጣሊያን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የኖርዌይ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር በአዲስ አበባ መወያየታቸውን ጠቅሰዋል።

በውይይታቸው በሀገራቱ መካከል በፖለቲካ፣ በንግድና በኢንቨስትመንት ዘርፎች የቆየውን ትብብር ለማጠናከር በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ምክክር መደረጉንም አስረድተዋል።

በተመሳሳይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከተባበሩት መንግስታት የሶማሊያ ልዩ ልዑክ ጋር በአፍሪካ ቀንድ የሰላም ሁኔታ ዙሪያ መክረዋል።

በሌላ በኩል በሳዑዲ አረቢያ በችግር ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ወደ አገር ቤት ለመመለስ መንግሥት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑም ተገልጿል።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የሚመራ ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ ዜጎቹን እንዲመለሱ እየሰራ ነው ተብሏል።

በቅርቡ ኢትዮጵያን በመወከል በተለያዩ ሀገራት ለተመደቡ አምባሳደሮች ብሔራዊ ጥቅምን በሚያስጠብቅ መልኩ ስራቸውን እንዲሰሩ የሚያስችል የአቅም ግንባታ ስልጠናና መመሪያ መሰጠቱም በመግለጫው ተነስቷል።

በሩሲያና በዩክሬን መካከል ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ በዩክሬን ይኖሩ በነበሩ ኢትዮጵያውያንና ሌሎች አፍሪካውያን ድንበር እንዳይሻገሩ በዘር እና በቀለም መድልኦ እየተደረገባቸው ስለመሆኑ ተነስቷል።

ይህን ችግር ለመቅረፍ የኢትዮጵያ መንግሥት በአጎራባች አገራት ካሉ አምባሳደሮች ጋር በመስራት ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች አፍሪካውያን ጭምር ደህንነታቸው ተጠብቆ በሰላም ከዩክሬን እንዲወጡና ወደ አጎራባች ሀገራት እንዲገቡ እያደረገ መሆኑ ተገልጿል።

ሰሞኑን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት መጀመሩን ተከትሎ የግብጽ ሚዲያዎች ‘‘የሱዳኑ የመርሆዎች ስምምነት ተጥሷል’’ በሚል የሐሰት ዘገባዎችን እየሰሩ መሆናቸውንም አምባሳደር ዲና ሙፍቲ መናገራቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።

ስምምነቱ ህዳሴ ግድብ ኃይል እንዳያመነጭ የጣለው ክልከላ የለም፤ ይልቁንም የግድቡ ግንባታ እየተከናወነ ድርድሩ እንደሚካሄድ በግልፅ ያትታል ብለዋል አምባሳደሩ በመግለጫቸው።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.