Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ-አሶሳ መንገድ ላይ የፀጥታ ችግር እየፈጠሩ ባሉ የሸኔ ታጣቂዎች ላይ የተቀናጀ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ-አሶሳ መንገድ ላይ የፀጥታ ችግር እየፈጠሩ ባሉት የሸኔ ታጣቂዎች ላይ የተቀናጀ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ገለፀ።
 
የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መለስ በየነ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ዋና ከተማ አሶሳ በምዕራብ ወለጋ ወደ አዲስ አበባ በሚወስደው መንገድ ላይ አሸባሪው ሸኔ ባለፉት ሁለት ዓመታት የፀጥታ ስጋት ሆኖ ቆይቷል።
 
ይህን ተከትሎም የክልሉ ነዋሪዎች ወደ መዲናዋ አዲስ አበባ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከመስተጓጎሉ ባለፈ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ቀውስ እያስከተለ መሆኑን ነው የተናገሩት።
 
በተለይም በፀጥታ ስጋቱ ከአዲስ አበባ የሚመጡ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች አቅርቦት መስተጓጎሉን አመልክተዋል።
 
አሁን ላይ ችግሩን ለማስወገድ የክልሉ መንግስት ከፌደራል፣ ኦሮሚያ እና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ጋር በመሆን የተጠናከረ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን አስታውቀዋል።
 
በእስካሁኑ ጥረቶች የሚፈለገው ለውጥ ያልመጣበትን ምክንያት በመገምገም በቀጣይ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም የፌዴራል መንግስት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በበለጠ ትኩረት እና ቅንጅት እንዲሰራም ነው የክልሉ መንግስት የጠየቀው።
 
በመላኩ ገደፍ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.