Fana: At a Speed of Life!

አቶ አገኘሁ ተሻገር ከወቅቱ የአሴካ ፕሬዝዳንት ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ከአሴካ (የአፍሪካና የአረቡ አለም አቻ ምክር ቤቶች) የወቅቱ ፕሬዚዳንት ኢናም ማያራ ጋር በኢንቨስትመንት ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

ውይይቱ በሞሮኮ ራባት ከተማ እየተካሄደ ከሚገኘው በ11ኛው የአሴካ ጉባዔ ጎን ለጎን የተካሄደ ነው ተብሏል።

አቶ አገኘሁ ተሻገር ከፕሬዚዳንቱ ጋር በነበራቸው ውይይትም ሞሮኮና ኢትዮጵያ ረዘም ላለ ጊዜ ጠንካራ ግንኙነት እንዳለቸው ገልፀው ሁለቱ ሀገራት በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምስረታ ላይ የነበራቸው ሚና የጎላ መሆኑን አንስተዋል::

በተጨማሪ ሞሮኮና ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ፥ በንግድ፥ በኢንቨስትመንት፥ በሳይንስና ቴክኖሎጂ እና መሰል መስኮች ጠንከር ያለግንኙነት እንዳላቸው ለፕሬዚዳንቱ ገልፀው ይህን ግንኙነት ሀገራችን ኢትዮጵያ አጠናክራ መቀጠል እንደምትፈልግ ለፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል::

በተለይም ያለውን ግንኙነት አስመልክተው አፈጉባዔው ሞሮኮ በኢትዮጵያ የአፈር ማዳበሪያ ለማምረት ያቀደችውን አጠናክራ እንድትቀጥል ኢትዮጵያ ፍላጎት አላት ብለዋል::

ፕሬዚዳንቱ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ በአፍሪካ ጉዳዮች የመሪነት ሚና ስትጫወት የቆየችና እየተጫወተች ያለች ሀገር መሆኗን አንስተው ከኢትዮጵያ ጋር ያለንን መልካም ግንኙነት አጠናክረን ለመቀጠል ፍላጎት አለን ሲሉ ተናግረዋል::

በኢትዮጵያ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካን ማቋቋም ብቻ ሳይሆን ይህን የአፈር ማዳበሪያ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ለማሰራጨትም ኢትዮጵያ ማዕከል እንድትሆን እንፈልጋለን ማለታቸውን ከፌደሬሽን ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በሲሚንቶ ምርት ላይ የመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀው፤ በዚህና ሌሎች ዘርፎች ያለንን ግንኙነቶች ይረዳ ዘንድ የተቀላጠፈ የቪዛ፣ የአየር በረራ እና መሰል አገልግሎቶች በሁለቱ ሀገራት መካከል እንዲኖር በትብብር ልንሰራ ይገባል ብለዋል::
ጉባዔው ዛሬም የቀጠለ ሲሆን÷ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ምክረ ሃሳብና አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.