Fana: At a Speed of Life!

የአማራ ብልፅግና ፓርቲ በብድር ስም የወጣው የፓርቲው ገንዘብ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከነ ወለዱ ታስቦ ተመላሽ እንዲደረግ ወሰነ

አበባ፣ የካቲት 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ብልፅግና ፓርቲ በብድር ስም የወጣው የፓርቲው ገንዘብ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከነ ወለዱ ታስቦ ተመላሽ እንዲደረግና ዝርዝር ሁኔታው ተጣርቶ የመጨረሻ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ በብድር ስም ገንዘብ የወሰዱ አመራርና ሰራተኞችም ከያዙት የመንግስትና የፓርቲ ኃላፊነት ከየካቲት 25/2014 ዓ.ም ጀምሮ እንዲነሱ መወሰኑን አስታወቀ።

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ፓርቲው መግለጫ አውጥቷል።

ሙሉ መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ከአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ለአመራርና ሰራተኞች ሲሰጥ የነበረን የገንዘብ ብድር በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ፤

የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ወቅታዊ ሁኔታውን ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ በየደረጃው ያለው አመራር የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት በመፍጠር ለዋናው ዓላማችን ስኬት ማለትም ለክልላችንና በአጠቃለይም ለሀገራችን ብልጽግና ተግቶ እየሰራ ይገኛል፡፡

ባለፉት ሦስት ዓመታት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተን ከሰራንባቸውና ጉልህ ስኬት ካስመዘገብንባቸው ጉዳዮች አንዱ ብቁ አመራርና የፓርቲ መዋቅር ለመገንባት የሰራነው ተግባር ነው፡፡
የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት በቀጣይነትም የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲውን በማጠናከር የፓርቲያችን አስተሳሰብ፣ አደረጃጃቱንና በአጠቃላይም አባላቱን ለማብቃት እየሰራ ይገኛል፡፡

በተጨማሪም ፓርቲያችን የአመራሩንና የአባላቱን ዕውቀት፣ ክህሎት፣ ጥበብና አቅም በተከታታይነት ለማብቃት ጥረት ከማድረጉም በላይ መታረም የሚገባቸውን የተቋም፣ የአመራርና የአባላት ጉድለቶች ጊዜ ሳይሰጣቸው እንዲታረሙ የማድረግ ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡

ይህን የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ የማጠናከር ስራ የምንሰራው ፓርቲያችን የተፈጠረው ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግ በመሆኑና የትኛውም ዓይነት መታረም ያለበት ተግባር በወቅቱ ካልታረመ የብልጽግና ጉዟችንን ያደናቅፋል የሚል ዕምነት ስላለን ነው፡፡

ከውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲ ማጠናከር ስራችን አንዱ የፓርቲውን አሰራርና መመሪያ ማጠናከርና ሳይሸራረፍ ተፈፃሚ ማድረግ ነው፡፡

በመሆኑም በአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት የፓርቲው ሃብት የሆነ ተቀማጭ ገንዘብ ለአመራሮችና ሰራተኞች የረጅም ጊዜ ብድር አሰራር ስርዓት በመዘርጋት ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በመዋዋል ሲከናወን መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ይኸው አሰራር ከፓርቲ የገንዘብና ሃብት አስተዳደር ስርዓት አኳያ ህገ ደንቡን የሚጣረስ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

የውሳኔ አሰጣጥና የስራው አፈፃፀም ከፓርቲው ህገ ደንብና አሰራር ጋር የሚቃረን መሆኑም ተረጋግጧል፡፡

በመሆኑም በብድር ስም የወጣው የፓርቲው ገንዘብ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከነ ወለዱ ታስቦ ተመላሽ እንዲደረግና ዝርዝር ሁኔታው ተጣርቶ የመጨረሻ ውሳኔ እስከሚሰጥ ድረስ በብድር ስም ገንዘብ የወሰዱ አመራርና ሰራተኞችም ከያዙት የመንግስትና የፓርቲ ኃላፊነት ከየካቲት 25/2014 ዓ.ም ጀምሮ እንዲነሱ ተደርጓል፡፡

ሆኖም ለአሰራሩ ተገዥ በመሆን ተፈፃሚ የማያደርጉ ግለሰቦች ካጋጠሙ በህጉ መሰረት ተጠያቂነታቸው የሚከናወን ይሆናል፡፡

ይህ የማጣራትና የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት በፓርቲው ህገ ደንብና አሰራር መሰረት በኦዲት ቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን መርማሪነት የውሳኔ ሃሳብ አቅራቢነት ተመስርቶ የክልሉ አስተባባሪ ኮሚቴ መርምሮ ውሳኔ የሰጠበት ሲሆን ዝርዝር ሁኔታው በፓርቲው የውስጥ አሰራር መሰረት ለመላ የፓርቲው አባላትና አመራሮች በተዋረድ በግልጽ ይፋ የሚደረግ ይሆናል፡፡
የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት
የካቲት 25/2014 ዓ.ም
ባህር ዳር

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.