Fana: At a Speed of Life!

የዓባይ ባንክ አጠቃላይ ሀብቱ 35 ቢሊየን ብር መድረሱን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓባይ ባንክ አጠቃላይ ሃብቱ 35 ቢሊየን ብር መድረሱን አስታወቀ፡፡
የባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ የኋላ ገሠሠ÷ በጎንደር ከተማ የዓባይ ባንክ ዲስትሪክት ስራ መጀመሩን አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር በከተማዋ የተሻለ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እንዲኖር ይሰራል ብለዋል፡፡
በ125 ሚሊየን ብር መነሻ ካፒታል ወደ ስራ የገባው ባንኩ÷ በአለፉት 11 ዓመታት አጠቃላይ የባንኩ ሀብት 35 ቢሊየን ብር መድረሱን ጨምረው ገልጸዋል፡፡
የባንኩ አጠቃላይ ቅርንጫፍ በሀገሪቱ 346 መድረሱን ጠቁመው÷ ሰባት ዲስትሪክቶች እንዳሉትም አመልክተዋል።
በጎንደር ቀጠና ያለውን ዕምቅ የኢንቨስትመንት አማራጭ ወደ ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለመቀየር በማሰብ ባንኩ በጎንደር ከተማ ዲስትሪክት እንዲከፈት መወሰኑንም ነው የተናገሩት፡፡
ለበርካታ ወጣቶች ባንኩ ሰፊ የስራ ዕድል መፍጠሩን የገለፁት ዋና ስራ አስፈፃሚው÷ ለተለያዩ ድርጅቶችና ተቋማት ባለሀብቶች የብድር አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።
ባንኩ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አሠራርን በመተግበር ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለደንበኞች በቅርበት እየሰጠ መሆኑም ተገልጿል።
በጎንደር ቀጠና ባንኩ በ32 ቅርንጫፎች አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዓባይ ባንክ የጎንደር ዲስትሪክት ስራ አስኪያጅ አቶ ቢራራ ሰማህኝ ናቸው፡፡
በጎንደር ከተማ ዲስትሪክቱ መከፈቱ ለብድር ፈላጊዎች በቅርበት አገልግሎት ከመስጠት በተጨማሪ በጦርነት የተቀዛቀዘውን የቀጠናውን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት አቅም ይፈጥራልም ብለዋል።
ባንኩ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ደንበኞች ያሉት ሲሆን÷ በአዲስ አበባ ባህርዳርና ደሴ ከተሞች ዘመናዊ ህንፃዎችን ለመገንባት ስራ መጀመሩም ተጠቅሷል፡፡
በምናለ አየነው
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.