Fana: At a Speed of Life!

ሻምበል ባሻ ሁሴን ጎበና፥ ብቻቸውን ክፍለ ጦር የገጠሙ የካራማራ ጀግና

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሻምበል ባሻ ሁሴን ጎበና ይህንን ታሪክ ሲሰሩ ገና የአሥር አለቃ ማዕረግ ላይ ነበሩ።

በቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት 25ኛ ሻለቃ ውስጥ በሞርታር ተኳሽነት ያሳዩት ድንቅ ብቃት ደግሞ ከሻለቃው የተወጣጡና 130 አባላት ወዳሉበት ኮማንዶ በአጭር ጊዜ እንዲቀላቀሉ አድርጓቸዋል።

ሻምበል ባሻ ሁሴን ከፋና ባልደረባ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳጫወቱት፥ በወቅቱ መተማ ከተማ ላይ ወረራ ተፈጽሞ ስለነበር፥ 25ኛ ሻለቃ ግዳጁን ለመወጣት ወደዚያው በመሄዱ ሻምበል ባሻ ሁሴንና የ130 ኮማንዶ አባላት ጠቅላይ የጦር ሰፈሩን እንዲጠብቁ ግዳጅ ተሰጣቸው።
ኮማንዶው የጦር ሰፈሩን ለመጠበቅ የታጠቀው መሳሪያ ደግሞ 50 ካሊበርና ቢ ኤም መሳሪያዎች ብቻ ነበሩ።

በዚህ መሃል ነበር የሶማሊያው መሪ የዚያድ ባሬ ጦር ኢትዮጵያን የወረረው። ሰገጉ የተባለችው የኢትዮጵያ ከተማ ደግሞ ወራሪው ኃይል ለመጀመሪያ ጊዜ የተቆጣጠራት ቦታ ነበረች።

በወቅቱ በስፍራው በነበረው የኢትዮጵያ ጦር ላይ የተፈፀመበት ድንገተኛ ጥቃት ስለነበር፥ ጥቃቱን ለመመከት እነ ሻምበል ባሻ ሁሴን የሚገኙበትና 130 አባላት ያሉት ኮማንዶ ወደ ስፍራው ተላከ።

የኮማንዶው ግንባር ቀደም ተልዕኮም ከወራሪው ኃይል ጥቃት የተረፈውን የወገን ጦር ከለላ በመስጠት ወደ ለጋ አመዞ ማምጣት በመሆኑ ፥ ተልዕኮውን ተቀብሎ ተንቀሳቀሰ። ነገር ግን ለወገን ጦር ድጋፍ የመስጠቱ ሂደት ቀላል አልነበረም። የዚያድ ባሬ ጦር በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ፊት እየገሰገሰ በመሆኑ በሁሉም መልኩ ጥንቃቄን የሚጠይቅ ነበር።

እነ ሻምበል ባሻ ሁሴን ጎበና የታጠቁት 50 ካሊበር መሳሪያና ኃይላቸውም 130 ወታደሮች በመሆኑ፥ ከባዱን ኦፕሬሽን የዳዊትና የጎልያድ ፍልሚያ አድርጎታል።

ይሁንና በኢትዮጵያ ፍቅር የተንቀለቀለው ወኔ ከጠላት ከፍተኛ ትጥቅ አንፃር ምንም የማይባልን መሳሪያ ቢይዝም፥ በሻምበል ባሻ ሁሴን ጎበና ፊት አውራሪነት የሚመራው የወገን ጦር በየመንገዱ የሚያገኘውን የጠላት ጦር አጭዶ ይከምረው ጀመር።

ሻምበል ባሻ ሁሴን እንደሚሉት፥ ለወገን ጦር ድጋፍ ለመስጠት ወደ ሰገጉ ያቀናው ኮማንዶው፥ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ባካሄደው ውጊያ ድልን አስመዝግቦ ለጋ አማዶ ደረሰ። በዚህ የሦስት ቀናት ጦርነት የኮማንዶው ሦስት አባላት ሲሰዉ፥ በአንፃሩ ከ1 ሺህ በላይ በሚሆን የጠላት ኃይል ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶ ለጋ አማዶ ደረሰ።

ለጋ አማዶ የኢትዮጵያ ጦር መልሶ ኃይሉን ማሰባሰብ የሚጀምርበት ቦታ ሆኖ በመመረጡ፥ የእነ ሻምበል ባሻ ኮማንዶ ለሌላ ግዳጅ ወደ ደጋህቡር አመራ። በደጋህቡር የጠላት ኃይል ለመፈንጨት እንዳይችል ያደረገው ክስተትም ተፈጠረ።

ለጋ አመዶ ላይ ወገንን የማደራጀትና መልሶ ወደ ውጊያ የማስገባት ስራ የሰራው ኮማንዶው ደገሀቡር ላይ ከተማዋን በፈንጂ በማጠር የመከላከል ጦርነት ማካሄድ ጀመረ።

ኮማንዶው በወቅቱ የመከላከል ጦርነት መምረጡ ካለው የሰውና የመሳሪያ ብዛት አንፃር ተገቢ እንደነበር ነው ሻምበል ባሻ ሁሴን የሚናገሩት።

“ጦርነቱ ተጀምሮ ጠላት ደገሀቡር ለመግባት በተጠመደ ፈንጂ ላይ ከብቶችን ለማስኬድ ቢሞክርም ከነበልባሎቹ የኢትዮጵያ ልጆች ጥይት ማምለጥ አልተቻለውም ነበር” ይላሉ ሻምበል ባሻ ። ነገር ግን በሀምሌ ወር የተለየ ክስተት ተፈጠረ። በወቅቱ ከአራት ጓዶቻቸው ጋር ወደ ደገሀቡር አውሮፕላን ማረፊያ አምርተው የነበሩት ሻምበል ባሻ ሁሴን ጎበና ከባድ መሣሪያ ተተኮሰባቸው።

በድንገተኛው ጥቃት የሻምበል ባሻ ሦስት ጓዶች ወዲያውኑ ህይወታቸው አለፈ። እርሳቸውም ከኮማንዶው በብዙ ርቀት ተቆርጠው ቀሩ።

በዚህ መሀል ነበር ሻምበል ባሻ ሁሴን ለብቻቸው ከአንድ ክፍለ ጦር ጋር መዋጋት የጀመሩት።

ብልሁ ወታደር ሻምበል ባሻ በፍጥነት ከሞቱ ወታደሮች ላይ ዘመናዊ መሳሪያዎችን በመታጠቅ ምሽግ ያዙ። አስቀድሞ በኮማንዶው የታጠረው ፈንጂ ፈንድቶ ያላለቀ በመሆኑ ወደ ሻምበል ባሻ ምሽግ እንደ ግሬሳ ወፍ ሆ ብሎ የሚመጣውን የጠላት ሰራዊት ይፈጀው ጀመር።

የወራሪው የዚያድ ባሬ ጦር ደገሀቡር ላይ ከባድ መሳሪያ በመተኮስ ጦርነቱን የጀመረው ከለሊቱ 10 ሰዓት እንደነበር የሚያስታወሱት ሻምበል ባሻ ሁሴን ፥ እስከ ቀኑ ሰባት ሰዓት በሻምበል ባሻና በወራሪው መካከል ውጊያው ቀጠለ።

በእግረኛ ጦር አልሳካለት ያለው ጠላትም 16 ታንኮችን አሰልፎ ሻምበል ባሻ ወደሚገኙበት ምሽግ አቀና። ይህን ጊዜ ከምሽጋቸው ሰብረው የወጡት ጀግናው ኢትዮጵያዊ፥ ሁለቱን ታንኮች ከጥቅም ውጪ ሲያደርጉ ሌሎቹን መማረክ ቻሉ።

የወራሪው ጦር ወታደሮች በአንድ ኢትዮጵያዊ ወታደር እንደ ቅጠል ሲረግፉ የተመለከተው የጠላት ክፍለ ጦር ኮለኔል፥ በሽምቅ ውጊያ የሻምበል ባሻን ምሽግ ለመስበር አቅዶ ተንቀሳቀሰ። ከቀኑ አምስት ሰዓት አንድ ጋዜጠኛና ሁለት ከፍተኛ አመራሮችን ይዞ በጀርባ በኩል ቢመጣም ትከሻውን ተመትቶ በእጃቸው መማረኩንም ነው ሻምበል ባሻ ሁሴን የሚያወሱት።

በዚህ መሀል ሻምበል ባሻ ተቆርጠው የቀሩበት ኮማንዶ ከሌሎች የኢትዮጵያ ኃይሎች ጋር በመሆን ቆረጣውን ሰብሮ ጠላትን አይቀጡ ቅጣት ቀጣው። ጀግናው የኢትዮጵያ ልጅ ሻምበል ባሻ ሁሴን ጎበናም ምርኳቸውን ለወገን ጦር አስረከቡ።

ሻምበል ባሻ ከዚያ በኋላም ወደ ጂግጂጋ በማቅናት ጠላትን ተፋልመዋል። በተለይም በከተማዋ በተለምዶ ውሃ ልማት ተብሎ የሚጠራው አካባቢ ሰርጎ ለመግባት የሞከረውን ጠላት ኮማንዶውን በማስተባበር ድባቅ መትተው ወደ ሀረር አቅንተዋል።

በሀረር የተወሰኑ ቦታዎች ኃይሉን አስርጎ የነበረው የጠላት ጦርም ክፉኛ ተመታ፤ በአጠቃላይም የዛሬ 44 ዓመት ወራሪ የፈጸመው የዚያድ ባሬ ጦር እንደ ሻምበል ባሻ ሁሴን ጎበና ባሉ የኢትዮጵያ ጅግኖች አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ ወደ መጣበት እንዲመለስ ተደርጓል።

በእዮናዳብ አንዱዓለም

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.