Fana: At a Speed of Life!

አዲስ ተሿሚ አምባሳደሮች በዜጎች ለሚቀርቡ የአገልግሎት ጥያቄዎች ፈጠን ምላሽ መስጠት አለባቸው – አምባሳደር ብርቱካን አያኖ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲስ ተሿሚ አምባሳደሮች ዘመናዊ የአሰራር ስርዓቶችን በመጠቀም ዜጎች ለሚያቀርቧቸው የአገልግሎት ጥያቄዎች ፈጠን ምላሽ መስጠት እንዳለባቸው የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ አሳሰቡ።

አምባሳደሮች በኢምባሲዎች እና ቆንስላ ጽፈት ቤት የሚከናወኑ አገልግሎቶች በሰነድና ዜግነት ማጣራት ምርመራ ሥራ ላይ በቂ እዉቀት፣ ክህሎት እና የተጠናከረ የቡድን ሥራ አስተሳሰብ እንዲኖር እና ስራውን አስተማማኝ ሁኔታ እንዲፈፅም መስራት እንዳለባቸውም አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ተናግረዋል።

የኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ታምሩ ገበቶ በበኩላቸው፥ በዉጭ አገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና የውጭ አገር ዜጎች የሚፈልጓቸውን አገልግሎቶች በጥንቃቄ ማጣራት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
በወሳኝ ኩነት መረጃ አሰባሰብ ስርዓት እና አደረጃጀት ዙሪያም ገለፃ የተደረገ መሆኑ ታውቋል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቆንስላ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል የሰነድ ማረጋገጥ ተ/ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል አየነው በበኩላቸው፥ ከዉጭ ሀገር ወደ አገር ቤት እና ከአገር ውስጥ ወደ ዉጭ የሚላኩ ሰነዶችን በማረጋገጥ ትክክለኛነታቸዉን የማጣራት ሥራዎች በጥራት እንዲፈፀሙ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።

በወቅቱም የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ኡጋ የቱሪዝም የልማት ቦታዎችን እና አቅሞችን በተመለከተ ለአምባሳደሮቹ ገለጻ ማድረጋቸው ተገልጿል።

አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በኢምባሲዎች እና ቆንስላ ጽ/ቤቶች የሚሰጡ አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ ዘመናዊ አማራጮችንና አሰራሮችን በመተግበር ለዜጎች ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠትና ተገቢውን እርካታ ማረጋገጥ እንደሚገባ ማሳሰባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.