Fana: At a Speed of Life!

ከተማ አስተዳደሩ ከ1 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባቸውን የመንገድ ፕሮጀክቶች ተመረቁ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ1 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባቸውን የመንገድ ፕሮጀክቶች ተመረቁ፡፡
 
ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ አጠቃላይ ፕሮጀክቶቹን በመምራት የተመረቀ ሲሆን፥ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ቡዜና አልቃድር ም/ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ እና ሌሎች የከተማው ከፍተኛ አመራሮች መገኘታቸውን ከከንቲባ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
 
ግንባታቸው ተጠናቆ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክብርት ወ/ሮ አዳነች አበቤ እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ከተመረቁት ፕሮጀክቶች መካከል 9 መንገዶች ፣ 2 የመኪና ማቆሚያዎች፣ የእግረኛ መንገዶች፣ የመንገድ ዳር መብራቶችን እና የእንጦጦ አምባ ት/ቤት የአስተዳደር ህንፃ ይገኙበታል፡፡
 
እነዚህ የመንገድ ፕሮጀክቶች የእግረኛ መንገዶችንና የመኪና ማቆሚያዎችን ሳይጨምር 19.12 ኪ.ሜ ርዝመት እና ከ13 እስከ 60 ሜትር የሚደርስ የጎን ስፋት አላቸው፡፡
 
ከፕሮጀክቶቹ መካከል የመኪና ማቆሚያዎችን ጨምሮ 8 የሚሆኑት በከተማ አስተዳደሩ በራስ አቅም የተገነቡ ሲሆን፥ ቀሪዎቹ በተለያዩ የስራ ተቋራጮች ተገንብተው የተጠናቀቁ ናቸው፡፡
 
ከንቲባ ኣዳነች አቤቤ በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ እንደገለፁት ፥ ፕሮጀክት መጀመር ብቻ ሳይሆን ጀምረን መጨረስ እንደምንችል የዛሬዎቹ ፕሮጀክቶች ማሳያ ናቸው ብለዋል፡፡
 
እነኚህን ሰራዎች ማከናወን የቻልነው በፈተና ውስጥ ሆነን ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች ፥ በአንድ በኩል አገራችንን ከማፍረስ ለማዳን የከተማ አስተዳደሩ ህዝቡን በማንቀሳቀስ ለሰራዊታችን ድጋፍና ደጀን በመሆን እንዲሁም የከተማውን ፀጥታ በመጠበቅ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ከዚሁ ጎን ለጎን የልማት ስራዎቻችን በታቀደላቸው መሰረት እንዲከናወኑ በማድረግ ውጤታማ መሆን ችለናል በማለት ገልፀዋል፡፡
 
ይህንን ስንል ያሰብነውን ሁሉ አከናውነናል ማለት አይደለም ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ፥ ጀመርን እንጂ ገና አልጨረስንም፤ ከተማችንን ተወዳዳሪና ብቁ አገልግሎት መስጠት የምትችል ለማድረግ ብዙ ስራ ይጠበቅብናል፤ ተባብረን ከሰራን ከተጋን በሰላማዊ ሁኔታ ውስጥ በብዙ እጥፍ እናሳካዋለን በማለት ተናግረዋል፡፡
 
በምርቃት ስነስርዓቱ ላይ አስተያታቸውን የሰጡት የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሞገስ በበኩላቸው ፥ ባለፉት አራት አመታት በመንገድ መሰረተ ልማት የተገኙ ጠቃሚ ልምዶችን እንደ ግብዓት በመውሰድ እና የከተማዋን መሪ ፕላን መነሻ በማድረግ አዲስ አበባ ያላትን ድርብርብ የመዲናነት ሚና የሚመጥን እንዲሁም የከተማዋን ኢኮኖሚና ማህበራዊ እድገት የሚሸከም የመንገድ መሰረተ ልማት እውን ለማድረግ እየተረባረብን ነው ብለዋል፡፡
 
የተመረቁት መንገዶች ህብረተሰቡ በእንክብካቤ እንዲይዛቸውና እንዲጠብቃቸው ከንቲባ አዳነች አሳስበዋል፡፡
 
ህብረተሰቡም ለተሰሩት ፕሮጀክቶች ምስጋናውን በተወካዮቹ አማካኝነት በየአካባቢው ስጦታ በማበርከት ጭምር ገልጿል፡፡
 
በከተማ አስተዳደሩ ከተመረቁ የመንገድ ፕሮጀክቶች፦
 
ቁስቋም -እንጦጦ:- 4.3 ኪ.ሜ ርዝመትና የእግረኛ መንገድን ጨምሮ 16 ሜትርየጎን ስፋት፣
ሽሮ ሜዳ -ቁስቋም:- የመንገድ ፕሮጀክቱ አጠቃላይ 2.6 ኪ.ሜ ርዝመትና 30 ሜትር የጎን ስፋት፣
 
እንጦጦ መኪና ማቆሚያ 1 እና 2 :- 321 መኪናዎችን በአንድ ጊዜ ማስቆም የሚያስችሉ ሁለት የመኪና ማቆሚያዎች ጠቅላላ ስፋት 9600 ካሬ ሜትር ፣
 
ወሎ ሰፈር ኡራዔል:- አጠቃላይ 1.4 ኪሎ ሜትር 35 ሜትር የጎን ስፋት፣
 
ለገሃር-ዋሽግተን ዲሲ አደባበይ:- 1.56 ኪ.ሜ ርዝመትና 13 ሜትር የጎን ስፋት፣
 
ገርጂ ሮባ -መብራት ኃይል:- 973 ሜትር ርዝመትና 30 ሜትር ስፋት፣
 
ወይራ – ቤተል:- ወይራ- ቤቴል አስፋልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት 1.4 ኪ.ሜትር ርዝመት እና 20 ሜትር የጐን ስፋት፣
 
ራስ ደስታ ቀጨኔ:- 2.5 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 20 ሜትር የጎን ስፋት፣
 
ሃጫሉ ሁንዴሳ ጎዳና:- አጠቃላይ 4.5 ኪሎ ሜትር ርዝመትና የብስክሌት፣ የእግረኛ፣ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመርና የአረንጓዴ ስፍራዎችን አካቶ 1200 ሜትር የጎን ስፋት፣
 
የሲ ኤም ሲ ሚካኤል ተሻጋሪ ድልድይ፡- የመሻገሪያ ድልድዩ 680 ሜትር ርዝመትና 30 ሜትር የጎን ስፋት፣
 
እንጦጦ አምባ ት/ቤት፡- ግንባታው 513 ካሬ ሜትር ስፋት ላይ ያረፈ ባለሶስት ወለል የትምህር ቤት ህንፃ፣
 
የእግረኛ መንገዶች ፡- 11.8 ኪ.ሜ ርዝመትና 3.5 ኪሎ ሜትር የጎን ስፋት፣
 
የመንገድ መብራት፡- 614 የመንገድ ዳር መብራት ፖሎች እና 18 ከፍተኛ የመብራት ፓውዛ የተገጠመላቸው ማማዎችን ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡
 
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
 
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
 
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.