Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ብልጽግና ምስጢር መደመር ፣ መከባበር እና በጋራ መቆም ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 28 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብልጽግና ምስጢር መደመር ፣ መከባበር እና በጋራ መቆም ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለፁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በ5 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ተገንብቶ የተጠናቀቀውን እና የተለያዩ የብረታ ብረት ምርቶችን የሚያመርተውን አዳማ ቆርቆሮ ፋብሪካ ማስፋፊያን ዛሬ በመረቁበት ወቅት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባስተላለፉት መልዕክትም፥ የአዳማ ቆርቆሮ ፋብሪካ ከትንሽ ጀምሮ ወደ ትልቅነት የመድረስ ተምሳሌት ነው ብለዋል።

ዛሬ የተመረቀው የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ኢንዱስትሪዎቻችን በሀገር ውስጥ አስፈላጊ የግንባታ ግብአቶችን ለማምረት ያላቸውን ከፍተኛ ዐቅም የሚያሳይ መሆኑንም ገልጸዋል።

እንዲህ ያሉ ሀገር በቀል ሞዴሎችን ማበራከት የውጭ ምንዛሪ ወጪያችንን በእጅጉ ለመቀነስ እንደሚያስችልም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት ።

ፋብሪካው በ10 ዓመት ውስጥ ከአነስተኛ ኢንደስትሪ ወደ ከፍተኛ መሸጋገር ከቻለ ኢትዮጵያን በ10 ዓመት ውስጥ ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ ይቻላል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ።

ለዚህ ኢትዮጵያውያን ሁሉ መደጋገፍ አለባቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ÷ ነገር ግን ተናንቆ እና ተሰዳድቦ ኢትዮጵያን ማሳደግ ቀርቶ ኢትዮጵያን ማቆም አይቻልም ብለዋል፡፡

ተባብረንና ሰርትተን የበለጸገች ኢትዮጵያን እንይ ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ፋብሪካው ከውጭ የሚገቡ የብረታ ብረት ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጪን የሚያስቀር ነው ተብሏል።

ፈብሪካው በ2003 ዓ.ም በ40 ቢሊየን ብር ካፒታል ነበር ወደ ስራ የገባው ።

ስራ ሲጀምር በአመት የማምረት አቅሙ 30 ሺህ ቶን የነበረ ሲሆን÷ ወደ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ቶን አድጓል ነው የተባለው።

ፋብሪካው በሙሉ አቅሙ ሲያመርት ለ3 ሺህ ሰዎች የስራ እድል እንደሚፈጥርም ነው የተገለጸው።

 

በአላዛር ታደለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.