Fana: At a Speed of Life!

ጃፓን የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ግቡን እንዲመታ አስፈላጊውን ድጋፍ ታደርጋለች- የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር የታለመለትን ግብ እንዲመታ ጃፓን አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ ገለጹ።

የኢትዮጵያ መንግሥት በአገሪቱ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር የሚያደርጋቸውን ጥረቶች ጃፓን በአድናቆት ትመለከተዋለች ብለዋል።

ጃፓን በታሪኳ የገጠማትን ፖለቲካዊ ምስቅልቅል በተለያዩ ምክክሮች ማለፏን አስታውሰው፥ ይህም ከሠላሟ አልፎ አሁን ለደረሰችበት የኢኮኖሚ እድገት መሰረት መጣሉን ገልጸዋል።

አገራቸው ከበርካታ ዓመታት በፊት በተከሰተው የእርስ በርስ ጦርነት በማኅበረሰቦች መካከል ትልቅ ቁርሾ መፍጠሩን ጠቁመው፥ ያንን አስከፊ ታሪክ በእርቅ መደምደማቸውን አስረድተዋል።

በእርስ በርስ ጦርነቱ በርካታ ሰዎች ቢሞቱም፣ ተጎጂዎች ቢኖሩም በእርቅና በመቻቻል ጃፓን ያንን ሁሉ አልፋ ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገሯን የአገራቸውን ታሪክ ለተሞክሮ አንስተው አብራርተዋል።
በኢትዮጵያም የሚካሄደው አገራዊ ምክክር ለኢትዮጵያ ህዝብ በርካታ ጥቅም ይዞ እንደሚመጣ ያላቸውን እምነት ጠቁመው፥ በሂደቱ ሁሉም ሊሳተፉ እንደሚገባ ገልጸዋል።

በተለይም በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ አገራዊ ምክክሩ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተናግረው÷ አገራዊ ምክክሩ የታለመለትን ግብ እንዲመታ ጃፓን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ ነው አምባሳደር ኢቶ ታካኮ ያረጋገጡት።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከውጭ ጣልቃ ገብነት ነጻ የሆነ አገራዊ ምክክር ለማካሄድ ፍላጎት እንዳለው አምናለሁ ብለዋል፡፡

በምክክር ሂደቱ ጃፓን ድጋፍ ማድረግ በምትችልባቸው ጉዳዮች ላይ ግን ትብብር ለማድረግ ዝግጁ ነች ብለዋል።

በሌላ በኩል ጃፓን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ የዘርፉ ተዋናዮች ጋር ውይይት እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

የጃፓን ኢንቨስተሮች ወደ ኢትዮጵያ በስፋት እንዲመጡ ጄትሮ በተሰኘው የጃፓን የውጭና የገቢ ንግድ ተቋም በኩል በኢትዮጵያ ያለውን የንግድና የኢንቨስትመንት አማራጮችን የማስተዋወቅ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።

በሌላ በኩል ጃፓን በዘላቂ ልማት ግቦች፣ በተለይም ደግሞ በግብርና ልማት በኃይል አቅርቦት ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመሥራት ፍላጎት እንዳላቸው አምባሳደሩ አረጋግጠዋል።

ዘንድሮ 50ኛ ዓመቱን የሚይዘው የጃፓን ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫም ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በውይይት የሚወሰን መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.