Fana: At a Speed of Life!

ዓለም አቀፉ የስራ ድርጅት ኢትዮጵያ በስራ እድል ፈጠራ ለምታከናውናቸው ተግባራት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፉ የስራ ድርጅት ኢትዮጵያ በስራ እድል ፈጠራ ለምታከናውናቸው ተግባራት የሚያደርገውን የቴክኒክ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ።
ድርጅቱ ከኢትዮጵያ መንገድ አስተዳደር ጋር በመተባበር በስራ ፈጠራ ላይ ያተኮረ በቢሾፍቱ እያካሄደ ባለው አውደ ጥናት እንደተመላከተው÷ በዋናነት በኢትዮጵያ የመንገድ መሰረተ ልማትን ለማስፋፋት በማሽነሪ ከሚሰሩ ስራዎች በተጓዳኝ በቴክኖሎጂን በመታገዝ በሰው ኃይል ሊከናወኑ የሚችሉ ተግባራትን ለማመላከት ያለመ ነው፡፡
በዓለም አቀፉ የስራ ድርጅት የኢትዮጵያና የአፍሪካ ቀንድ አገራት ዳይሬክተር አሌክሶ ሙሲንዶ እንዳሉት÷ የዓለም የስራ ድርጅት ኢትዮጵያ በስራ እድል ፈጠራ ለምታከናውነው ተግባር የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል።
በኢትዮጵያ የመንገድ ግንባታ በሚከናወንባቸው አካባቢዎች ለሚኖሩ የኀብረተሰብ ክፍሎች ስልጠና በመስጠት በርካታ የስራ እድል መፍጠር እንደሚቻል ጠቁመው÷ ድርጅታቸው ለዚሁ ስራ ቴክኒካል ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ መንገድ አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር የትምጌታ አስራት በበኩላቸው÷ በፌዴራል መንግስት በተያዙ የመንገድ ፕሮጀክቶች ብቻ በየዓመቱ ከ100 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጠር ጠቁመዋል።
በዓለም አቀፉ የስራ ድርጅት የማህበረሰብ ስራ የፖሊሲ አማካሪው አስፋው ኪዳኑ÷ ሰፊ የስራ ዕድል መፍጠር ከሚቻልባቸው ዘርፎች አንዱ የመንገድ ግንባታ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት እድገትና ብልጽግናን ለማምጣት በሚተገብራቸው ፕሮጀክቶች በከፍተኛ ማሽን ከሚከናወኑ ስራዎች በተጨማሪ አጫጭር ስልጠናዎችን በመስጠትና ቴክኖሎጂን በመጠቀም ለበርካታ ሰዎች የስራ እድል መፍጠር እንደሚቻል አመላክተዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.