Fana: At a Speed of Life!

ናዝራዊት አበራን በቻይና ዕፅ በማዘዋወር ወንጀል ለእስር እንድትዳረግ ምክንያት በሆነችው ጓደኛዋ ላይ ውሳኔ ተላለፈ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2014 (ኤፍ ቢሲ) ናዝራዊት አበራ በቻይና አገር ያለአግባብ ዕፅ ከማዘዋወር ጋር በተያያዘ እንድትከሰስና ለእስራት እንድትዳረግ ምክንያት በሆነችው ጓደኛዋ ላይ የቅጣት ውሳኔ ተላለፈባት::
 
ስምረት ካህሳይ አንተሀቡ የተባለችው ተከሳሽ ልዩ ፍቃድ ሳይኖራት በህዳር ወር 2011 ዓ.ም ወደ አገር ያስገባችውን 5 በሻምፖ እቃ የታሸገ ኮኬይን ዕፅ ተበዳይ ናዝራዊት አበራ የተባለች ጓደኛዋን ወደ ቻይና አብረን እንሂድ ብላ በማግባባት ቪዛ እና የአየር ትኬት ካስጨረሰች በኋላ ታህሳስ 11 ቀን 2011 ዓ.ም ለናዝራዊት አበራ ሰው ሰራሽ ጸጉር ማጠቢያ ነው ቻይና ውሰጅልኝ ካለቻት በኋላ እርሷ ግን የአባቷን ሞት ምክንያት በማድረግ ትቀራለች፡፡
 
ተበዳይ ናዝራዊት አበራም ቻይና ደርሳ አውሮፕላን ማረፊያ በተደረገባት ፍተሻ የያዘችው 5 ሻምፖ መሰል 5 ኪሎ ግራም የሚመዝን የኮኬይን ዕፅ መሆኑ ተደርሶበት ለእስር አንድትዳረግ ምክንያት በመሆኗ ተከሳሽ ሁኔታውን ያልተገነዘበችን ሰው በመጠቀም በፈፀመችው መርዛማ ወይም የናርኮቲክና ሳይኮትሮፒክ እፆችን ወደ ውጪ አገር መላክ ወይም ማዘዋወር ወንጀል በዐቃቤ ህግ ክስ ተመስርቶባታል፡፡
 
በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎት ተከሳሽ ቀርባና ክሱ ተነቦላት “በዐቃቤ ህግ የተመሰረተብኝን ክስ ተረድቸዋለሁ ፤በተመሰረተብኝ ክስ ግን ጥፋተኛ አይደለሁም፤ ምክንያቱም ለጓደኛዬ ለናዝራዊት አበራ የሰጠኋት የኮኬይን ዕፅ ሳይሆን የፀጉር መታጠቢያ ሻምፖ ነው፤ በዚህም ጥፋተኛ አይደለሁም” ስትል የእምነት ክህደት ቃሏን ሰጥታለች።
 
ዐቃቤ ህግ በበኩሉ÷ የተከሳሽን ጥፋተኝነት የሚያስረዱ 8 የሰው፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከኢሜግሬሽን ዜግነትና የወሳኝ ኩነት ኤጄንሲ የተገኙ ዝርዝር የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቧል፡፡
 
ይህ ስጋት የገባት ስምረት ካህሳይም የማስረጃውን ሁኔታ ጥፋተኝነቷን በጉልህ ማሳየቱን ስትረዳ የሚቀጥለውን ቀጠሮ በመፍራት ከቅጣት እንደማታመልጥ ሲገባት ለጊዜው መሰወሯ ተመላክቷል፡፡
 
በከሳሽ ዐቃቤ ህግና በተከሳሽ ስምረት ካህሳይ መካከል የተደረገውን ክርክር ሲያዳምጥ የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ወንጀል ችሎትም ዐቃቤ ህግ ባቀረበው ክስ እና ማስረጃ መሰረት ተከሳሽ ጥፋተኛ መሆኗ በበቂ ሁኔታ መረጋገጡን አንስቷል፡፡
 
ፍርድ ቤቱ ተከሳሽ ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ ለመስጠት የካቲት 25 ቀን 2014 ዓ.ም በዋለው ችሎትም ተከሳሽ በ15 ዓመት እስራትና በ100 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንድትቀጣ ወስኗል፡፡
 
የኢሚግሬሽን ዜግነት የወሳኝ ኩነት ኤጄንሲ ተከሳሽ ስምረት ካህሳይን ወደ ውጭጪ አገር ስትወጣ ወይም ወደ አገር ውስጥ ስትገባ ተከታትሎ በመድረስ ለፌደራል ፖሊስ አሳልፎ እንዲሰጥና የፌደራል ፖሊስም ተከሳሿን አፈላልጎ ለማረሚያ ቤት እንዲያስረክብ ትዕዛዝ በመስጠት መዝገቡ መዘጋቱን ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
 
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
 
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.