Fana: At a Speed of Life!

በባሌ ዞን ከ113 ሚሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ አርሶና አርብቶ አደሮች ወደ ባለሀብትነት ተሸጋገሩ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በባሌ ዞን ከ113 ሚሊየን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 21 ግንባር ቀደም አርሶና አርብቶ አደሮች ወደ ባለሃብትነት መሸጋገራቸውን የሚያረጋግጥ እውቅና ተሰጣቸው።

ዛሬ በተሰጠው የእውቅና አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት ላይ ወደ ባለሃብትነት የተሸጋገሩት አርሶ አርብቶ አደሮች ከዞኑ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ጽህፈት ቤት ጋር የመግባቢያ ሰነድ በባሌ ሮቤ ከተማ ተፈራርመዋል፡፡

የዞኑ ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ሰዓዳ ኢስማኤል በወቅቱ እንደገለጹት ፥ ግንባር ቀደም አርሶና አርብቶ አደሮች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሰማሩ ለማስቻል በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

ዛሬ ወደ ባለሃብትነት እንዲሸጋገሩ እውቅና የተሰጣቸው አርሶ አደሮች እያንዳንዳቸው ከ1 ነጥብ 5 እስከ 20 ሚሊየን የመነሻ ካፒታል ያስመዘገቡ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

በግብርና፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በአገልግሎት፣ በማኑፋክቸሪንግና ሌሎች መስኮች ለመሰማራት የስራ ዕቅድ ያቀረቡት አርሶና አርብቶ አደሮቹ ከ1ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥሩ ይጠበቃል።

ለኢንቨስትመንት የሚውል ከ100 በላይ ሄክታር መሬት ለአርሶና አርብቶ አደሮቹ መዘጋጀቱን የተናገሩት ሃላፊዋ ፥ እነዚህም ከ113 ሚሊየን ብር በላይ አጠቃላይ ካፒታል ያስመዘገቡ መሆናቸውን ይፋ አድርገዋል።

ወደ ኢንቨስትመንት የተሸጋገሩት አርሶና አርብቶ አደሮች በቴክኖሎጂ፣ በግብዓት አቅርቦትና በፋይናንስ አስፈላጊው ድጋፍ ሁሉ ያገኛሉ ብለዋል።

መንግስት የግብርና ዘርፉን ከማዘመን ባለፈ ወደ ባለሃብትነት ለሚሸጋገሩ አርሶና አርብቶ አደሮች የመካናይዜሽን መሳሪያዎች፣ የፋይናንስ አቅርቦትና ከቀረጥ ነፃ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን እንዲያስገቡ እያደረገ መሆኑንም ወይዘሮ ሰዓዳ ተናግረዋል።

ወደ ባለሃብትነት ከተሸጋገሩት መካከል አቶ ኑራ ኢስማኤል በሰጡት አስተያየት ፥ ከ5 ሚሊየን ብር በላይ ካፒታል በማስመዝገብ ወደ ባለሃብትነት እንደተሸጋገሩ እውቅና ማግኘታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በማደያና የሆቴል አገልግሎት ዘርፍ ለመሰማራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ከጽህፈት ቤቱ ጋር መፈራረማቸውን አረጋግጠዋል።

ከቆየ የግብርና ስራ ተሞክሯቸው በመነሳት ከምግብ ፍጆታ ባለፈ ገበያ ተኮር ምርት በማምረት እሴት በመጨመር በቀጥታ ወደ ውጭ ለመላክ ዕቅድ አቅርበው ፥ ለዚህም እውቅና አግኝተዋል።

በማሾ፣ ቦሎቄና ሌሎች ገበያ ተኮር ምርቶች ላይ ለመሰማራት መዘጋጀታቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላው ወደ ባለሃብትነት የተሸጋገሩት አቶ ኡመር ሀሰን ናቸው፡፡

ባለፉት ዓመታት በተሰማሩበት የግብርና ስራ ውጤታማ በመሆናቸው ከሚያገኙት ገቢ ላይ በመቆጠብ 6 ሚሊየን ብር ካፒታል ማስመዝገባቸውን ተናግረዋል፡፡

በባሌ ዞን አሁን ላይ ከ2 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል አስመዝግበው በተለያዩ የልማት መስኮች የተሰማሩ 145 ባለሃብቶች ለ28ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠራቸውን ከዞኑ ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.