ብልጽግና ፓርቲ ነገ በሚጀምረው ጉባኤው የኢትዮጵያውያንን ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚያረጋግጡ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉ አስታወቀ
አዲስ አበባ፣መጋቢት 1፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ብልጽግና ፓርቲ ነገ በሚጀምረው ጉባኤ የኢትዮጵያውያንን ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚያረጋግጡ ውሳኔዎች ይተላለፍበታል አለ።
ጉባኤውን አስመልክቶ የፓርቲው የህዝብና ዓለም አቀፍ ግኑኝነት ዘርፍ ሀላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ መግለጫ ሰጥተዋል።
ዶክተር ቢቂላ የብልጽግና አንደኛ ጉባኤ ባለፉት ሶስት አመታት ፓርቲው በሁሉም መስክ የተጎናጸፋቸውን ድሎች ይገመግማል ብለዋል።
የገጠሙትን ችግሮች እና ተግዳሮቶች በጥልቀት ገምግሞ ለማረም ታሪካዊ ውሳኔ ያሳልፋልም ብለዋል።
ጉባኤው በጸጥታ ሁኔታ፣ በኢኮኖሚ እንዲሁም በሀገረ መንግስት ግንባታ ላይ ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚመክርም ገልጸዋል።
በዚህም ለዜጎች ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚያመጡ ውሳኔዎች ይተላለፋሉ ነው ያሉት።
የብልጽግና ፓርቲ አንደኛ ጉባኤ ነገ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ይጀምራል።
በጉባኤው 1 ሺህ 600 የፓርቲው አባላት በድምፅ የሚሳተፉ ሲሆን፥ 400 ከተለያየ የህብረተሰብ ክፍሎች እና ከውጭ ሀገራት የተጋበዙ እንግዶች ያለ ድምፅ ይሳተፋሉ።
ጉባኤው የፓርቲው አመራሮች፣ አባላት እና ደጋፊዎች የአስተሳሰብ እና የተግባር አንድነት የሚጎናጸፉበት፣ ፓርቲው በአደረጃጀት እና አሰራር ራሱን የሚያጠናክርበት እንዲሁም ፓርቲውን ሊያሻግሩ እና የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ሊያረጋግጡ የሚችሉ ጠንካራ የፓርቲ አመራሮች የሚመረጡበትም ይሆናል ብለዋል።
በአልአዛር ታደለ